Daily Archives: 17 April, 2013

ተበድለን ይቅርታ አንጠይቅም!

አብዶ ኑር የሱፍ (ኖርዌ)

ፍትህ እና የሰብዐዊ መብት ጉዳይ ህዝቡ እርሙን ባያወጣም ከተቀበሩ ከ 21 አመታት በላይ ሆኗቸዋል። ይህ ያለው መንግስት እነዚህ ለህዝብ የሚስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን በመቅበር ህዝቡ እንዳይተነፍስ በማድረግ አፍኖ መግዛቱን በማን አለብኝነት ተያይዞታል ። በሃገራችን ስለ መብት መጠየቅ ወንጀል ሆኗል ። ስለ መብት ደፍረው በሚጠይቁት ላይ የአሸባሪነት ታርጋ ይለጠፋል ፤ወደ ወህኒ ይወረወራሉ ፤ ከህግ ውጭ ኢ-ሰብዐዊ ግፎች ይፈጽምባቸዋል ፤ ከዛም አድርባይ ምሁር ነን ባዮችን በመጠቀም ተበዳዮች ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ ይደረጋል ።ይህ የተለመደ ሰላማዊ ታጋዮችን ከጨዋታ ውጭ ማድረጊያ መንገድ ነው ።

ልብ በሉ ይህ መንግስት የሽምግልና ባህላችንን ጭምር እንኳን ሳይቀር እያዋረደ ያለ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል ። ስለ ሽምግልና ካወራን ሽምግልና ማለት በሁለቱንም ወገን ግራ እና ቀኝ አይቶ ጥፋተኛው ጥፋቱን አምኖ ፤ ለተበደለው ወገን የበደሉን ካሳ ወይም የበደሉን ይቅርታ የሚቸርበት የተከበረ የሃገራችን ማህበራዊ እሴት ነበር ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ እየተደረገ ያለው የሽምግልና ሂደት ከባህላችን ወጣ ያለ ፤ግራ እና ቀኙን ያላመዛዘነ ፤ የመብት ጠያቂዎች የደረሰባቸውን የሰብዐዊ መብት ረገጣ ከግምት ዉስጥ ያላስገባ ነው ።እነዚህ ሽማግሌዎች የተበደሉ ታሳሪዎችን እራሳቸውን ጥፋተኛ አድርገው ይቅርታ እንዲጠይቁ በማግባባት ተግባር ላይ በመሰማራታቸው የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርጋቸውን ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ ።

በነገራችን ላይ በዚህ የሽምግልና አካሄድ ይቅርታ መጠየቅ በራሱ በምናነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ላይ እራሱን የቻለ ጉዳት አለው ። እንደ ባህላችን ያጠፋ አካል ካለ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው ። ነገር ግን ሽማግሌ በሚባሉት ግለሰቦች አማካኝነት ባልሰራኸው ስራ ይቅርታ ጠይቀህ ከእስር ቤት ስትወጣ ከመታሰርህ በፊት ስትታገልለት የነበረውን የመብት ጥያቄ ደግመህ መጠየቅ እንዳትችል መደረጉን እርግጠኛ መሆን አለብህ ። ምን ይህ ብቻ ያለ ጥፋትህ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ድምጽህን ማፈን ለሚፈልገው መንግስት የልብ ልብ መስጠት እና የሚያስፈራራ ድምጽ ያለው ቃጭል በአንገትህ ላይ ታስሮልህ እንደመንቀሳቀስ ያህል ይቆጠራል ።በዚህም አስፈሪ ድምጽ ምክንያት ደንብረህ የምታምንበትን የመብት ጥያቄ ከግብ ሳታደርስ እግሬ አውጭኝ ብለህ እንድትፈረጥጥ ወይም ዝምታን እንድትመርጥ ትገደዳለህ ።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ በሃገራችን የሰላማዊ ትግል ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ለማጠልሸት ብሎም ህዝበ ሙስሊሙ እየተከተለው ያለውን የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለማስቆም ይህ ተንኮለኛ መንግስት ራሱን የሙስሊም ምሁራን በማለት የሚጠራን አንድ ቡድን በመጠቀም የዘረጋው አዲስ ነገር የሚመስል ግን የተነቃበት አካሄድ ነው ።

ምስጋና የሚገባው ህዝብ!!!

ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ወገቡን አጥብቆ ለሀይማኖታዊ መብቱ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ከገባ ይኸው ሁለት አመት ሊሞላው እየተንደረደረ ነው፡፡ ሁለት የፈተና፣ የመከራ፣ የትግል፣ የበደል፣ ከምንም በላይ ደግሞ የሞራል ልእልና እና የበላይነት የተጎናጸፈበት አመታት ናቸው – የድልም! በዚህ ወቅት ውስጥ ይህ ድንቅ ትውልድ የታዩበት ባህርያት ዛሬ ለምስጋና ብእር እንድንነሳ አስገደደን፡፡ ለዚህ ህዝባችን ምስጋና በቂ ሆኖ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚመሰገንበት ውለታው ብዙ ነው፡፡ ጀዛው አላህ ዘንድ ነው፡፡ ግና መልካም ባህሪዎቹን እየጠቀሱ ጎልተው እንዲወጡ ማድረጉ ታሪካችንን ቀርጾ በማስቀመጡ ረገድ የሚጫወተው ሚና ይኖረዋል፡፡ ህዝባችን መልካም ባህሪዎቹን አውቆ እንዲያሳድጋቸው፣ እንዲያዳብራቸውም ያግዛል፡፡ ከመልካም ባህሪያቱ ንጻሬ ኋላ ደግሞ ድክመቶቹን ተመልክቶ በቻለው እንዲቀርፋቸው በር ይከፍታል፡፡ አንድ አንድ እያልን አብረን እያየናቸው

ህዝባችንን እናመስግን!
አንድነትን የመረጠ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

በትግላችን ውስጥ ጎልተው ከወጡ ህዝባዊ ባህርያት አንዱና ዋነኛው አንድነቱ ነው፡፡ የአህባሽ አደጋ ሙስሊሙን እንዲሰነጣጥቅ ታስቦ የመጣ ነበር፤ ግና የአላህ ፍላጎት ተቃራኒው ሆነና ጠንካራ የአንድነት መሰረት ይኖረን ዘንድ ተቻለ፡፡ ህዝባችን ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የአላህ ስጦታ የሆነው አንድነት መሰረቱ ከበፊቱ ጠንክሮ ይጣል ዘንድ ቀልቡን ለውህደት ከፍቷል፡፡ ጭቅጭቅና ልዩነት ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች በተቻለው በመራቅ በፍጹም መተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ወንድማዊ ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ መጅሊሱና ጸብ የመፍጠር አባዜ የያዛቸው አመራሮቹ በአንድነቱ ላይ የሚያደርጉትን ትንኮሳ በብስለት ዝቅ ብሎ አሳልፏል፡፡ አንድነቱን ለመበተን ያላደረጉት ጥረት፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ ግና አልቻሉም! ባለፉት ሁለት መውሊዶች በሙስሊሙ መካከል ክፍተት ለመፍጠርና ትግሉን ለማኮላሸት ያልተደረገ ጥረት አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ግን ‹‹መውሊድ አይከፋፍለንም›› ሲል አሳፈራቸው፡፡ በተወዳጁ ነቢይ ስም ሙስሊሞችን መነጣጠል እንደማይሳካላቸው አረጋገጠላቸው፡፡ ‹‹ወሐቢያ፣ ሱፊያ›› የሚሉ ስሞች በፓርላማ ጭምር ሲነሱ ሙስሊሙ ግን አንድነትን መርጦ ‹‹እኛ ሙስሊሞች ነን›› አላቸው፡፡ አልሐምዱሊላህ! አንድነታችንን ዘላቂና የጠለቀ ያደርግልን ዘንድ አላህን እንለምነዋለን! ለዚህ ድንቅ ባህሪውም ህዝባችንን እናመሰግናለን!