የሰላማዊ ትግላችን…ሰለማዊ ቦምቦች – ቁጥር 4

ሰዒድ ከድር

ባለፉት 3 ክፍሎች ስለ ዱዓ፡ መልካም ስነ ምግባርና የግለሰባዊ ሃላፊነትና ተጠያቂነት መንፈስ ማዳበር አይነተኛ የሰላማዊ ትግላችን መሳሪያዎች እንደሆኑ ለማየት ሞከረናል። ዛሬ በአላህ ፈቃድ ስለ “ፅናት” በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።

ቁጥር 4፡ *ፅናት*

ከሳምንት በፈት “ያን ቀን…የበረዶ ክፍሎቹ ይመሰክራሉ” የሚል አጥር ያለ ፅሁፍ አስነብቤ ነበር። በዚሁ ፅሁፍ ውስጥ ሙእሚኖች በዱኒያ ላይ ሲኖሩ በጣም ብዙ ፈተናዎች በሁሉም አቅጣጫዎች እንደሚደቀኑባቸው ለመጥቀስ ሞክሪያለሁ። ሙእሚኖቸ እነዚያንና ተመሰሳይ ፈተናዎቸን ለማለፍ ከሚያሰፍልጓቸው መሳሪያዎች አንዱ “ፅናት” ነው። ፅናት በአጭሩ ሲገለፅ ሰዎቸ የሆነን አላማ አስቀምጠው እርሱን እውን ለማድረግ በሚንቀሳቀሱበት ሰዓት ለሚያጋጥሟቸው እያንዳንዱ ፈተናዎች ያለምንም ወደሗላ መመለስ ፈተናዎቹን በጥበብና በትዕግስት አያለፉ አላማን ከግብ ማድረስ ወይም የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ማለት ነው። ሙስሊሞች ለአመኑበት ዲን ኢስላም መክፍል የሚገባቸወን መስዋፅትነት በፅናት ሲከፍሉ የተነሱለት አላማ እውን ይሆናል። የእኛ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም የአጭር ጊዜ ግባችን አሁን ከሚደርሱብን ዘርፈ ብዙ የመብት ረገጣዎቸና ሰብአዊ እንግልቶች ራሳችንን አላቀን በሀገራችን ላይ ሙሉ መብታችን ሳይሸራረፍ ተክበሮ በክብር መኖር ሲሆን ይህም መንገድ መክፍል የሚያሰፈልገውን መስዋዕት እየከፈሉ በፅናት እሰከመጨረሻው መቀጠልን ይጠይቃል። ሌላው የእኛ የሙስሊምች ትልቁና የረዥም ጊዜ ግባችን በሙስሊምነታችን (በእምነታችን) በምድር ላይ ቆይታችን የሚጋረጡብንን ብዙ ፈተናዎች ጠንቅቀን ተረድተን ፈተናዎቻችንን በፅናት መወጣት ነው። እርግጥ ነው! ምንም ሌሊቱ ቢረዝም መንጋቱ አይቀርም። በኢስልምናችን ላይ የሚመጣ አደጋ ምንም ያክል ዋጋ ቢያስከፍለንም ውድን ነገር.. “ጀነትን”… ለማገኘት እንጂ ለተራ ነገር ስላልሆነ ብዙም አይከብደንም…ኢንሻአላህ።

በጥቅሉ ፅናት ሁልጊዜ በህይወት ዑደታችን ውስጥ ከፊትለፊታችን የሚያጋጥሙንን አያሌ “መሰናክሎችን” ወደ ሰኬት ጓዳና “መረማመጃ ደረጃነት” ለመቀየር ፅናትን ይጠይቃል። ፅናት ለማንኛውም የህይወት እንቅስቃሴያችን ከግብ መድረስ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ትንሽም ይሁን ትልቅ ስራ ተጀምሮ ለመጨረስ ፅናትን ይጠይቃል። መልካም ስነ ምግባራችንን ለመገንባት የዘወትር ፅናት ይጠይቃል። እውቀትን ለማካበት ፅናት ያስፈልጋል። እምነትም በምላስ ተለፍፎ ብቻ ጣዕም እንደሌለው የኢስላም ታላላቅ ስብዕናዎች አስመስከረዋል። ብዙ ሶሃባዎች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ተደብድበው ተሰቃይተው ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ሁሉም የሚስማሙት ነገር ድብደባው ኢማናቸውን ጨመረላቸው እንጂ ወደ ሗላ አልመለሳቸውም። ፈተናው ቀላል ሆኖ ሳይሆን ጀነትን ለማግኝት መከፈል ያለበትም መስዋፅትነት ከባድ እንደሆነ ስለተረዱ እንጂ። ፈተና የሙዕሚኖችን ልብ ያረጋጋል እንጂ አይረብሽም። በኢማን ብርሃንም ይሞላል። የሙዕሚን ዱዓ ከኢማኔ በላይ አትፈትነኝ ነው እንጂ መቼም ቢሆን ፈተናን አርቅልኝ አይደለም። ያለ ፈተና እንዴት ጀነት ይገኛል? ይህ ሁሉ…ፅናትን…ይጠይቃል።

አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን ውስጥ ስለ ፅናት በብዙ ቦታዎቸ ከትዕግስት ጋር እያቆራኘ ይገልፃል። እስኪ የተውስኑትን አንቀፆች እንመልከት፦

“ እነዚያ “ጌታችን አላህ ነው” ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ “አትፍሩ፡አትዘኑም በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ” በማለት በነሱ ላይ መላዕክት ይወርዳሉ።” (41፡30)

“አላህ እነዚያን ያመኑትን በቅርቢቱም ህይወት፡በመጨረሻይቱም በተረጋገጠው ቃል ላይ ያረጋቸዋል።…”(14፡270)

“ለጌታህም (ትዕዛዝ) ታገስ።” (74፡7)

“ከችግርም ጋር ምቾት አለ። ከችግር ጋር በእርግጥ ምቾት አለ።” (94፡5-6)

ዛሬ የኢትዩጵያ ሙስሊሞች ላይ በጣም ካባድ ፈተና ተደቅኗል። ወጣቶች ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ በየጫካው እየተሰደዱ ነው። ሰዎች እየተገረፉ እየተደበደቡ ነው።ግለሰባዊ ህይዎታቸው እንኳን በቤታቸው ውስጥ ሳይቀር ሰላም ተነፍጎታል። ንብረታቸውም እየተዘረፈ ነው። ሙስሊሞች በቀንም በሌሊትም እየተሸበሩ ነው “ለሰላም ቀናኢ” በሆነው መንግስታችን! ብዙ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳትም እየደረሰባቸው ነው።… ሁልጊዜም የማይቀየረ አንድ እውነታ ግን አለ። ይኸውም መጨረሻው…ለእውነተኞችና አላህን ፈሪዎች መሆኑ። ይህ ጉዳይ ዘመን የማይሸረው እውነት ነው። እመኑ እውነትነ የያዙ ህዝቦች አሸናፊዎች ናቸው። ከአላህ በላይ ንግግሩ ታማኝ ማነው? ወላሂ! ማንም። አላህ በቁርአኑ…በማይነጥፈውና በህያው ቃሉ እንዲህ ብሎናል፦

“ ሙሳ ለሰዎቹ፦ “ለአላህ ተገዙ ታገሱም። ምድር ለአላህ ናትና። ከባሮቹ ለሚሻው ያወርሳታል። ምስጉንዋም ፍፃሜ ለጥንቁቆች (አላህን ፈሪዎች) ናት” አላቸው።” (7፡128)

“ቤተሰብህንም በስግደት እዘዝ። በእርሷም ላይ ዘወትር (ፅና)። ሲሳይን አንጠይቅህም።እኛ እንሰጥሃለን። መልካሚቱም መጨረሻም ለጥንቁቆቹ (አላህን ፈሪዎቹ) ናት።” (20፡132)

“…በችግር በበሸታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)። እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው። እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ (አላህን ፈሪዎቹ) እነርሱ ናቸው።”(2፡177)

ሰለማዊ ትግላችን የብዙ ህይወቶችን ዋጋ እያስከፈለን ቢሆንም መጨረሻ ግን አሸናፊዎቹ እኛው ነን። እውነት ከእኛ ጋ ስለሆነች…ኢንሻአላህ፡፤

ፅናትን ለማዳበር የሚረዱን ነገሮች፦
1) ቁርአንን ማንበብ ማሰተንተን
2) መልካም መስራት ከመጥፎ መከልከል
3) ሱና ነገሮችን ማዘውተር
4) የነቢያቶችንና የሶሃባዎችን ታሪክ ማንበብና መከተል
5) ዱዓ
6) ዚክር (አላህነ አብዝቶ ማውሳት)
7) ስልጠናዎችን በመውሰድም ሆነ ኢስላማዊ እውቀትን በመማር ፅናትን ማዳበር
8) ኢስልምና የክብራችንና የማነነታችን መሰረት መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ
9) ከጠንካራ ሙእሚኖች ጋር ጓደኝነት መፍጠር
10) የአላሀ እርዳት ሁለጊዜም እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን
11) የውሸተን ምንነት ጠንቅቆ መረዳትና የእውነትን ዋጋ መገንዘብ
12) የትልልቅ ኡለማዎቻችንን ምክር መቀበል
13) አሚሮቻችንን መታዘዝ
14) ፅናትን የሚያላብሱ ባህሪያቶችን ማወቅና መተግበር
15) ስለ ጀነት ድሎት ማሰብ፡ስለ ጀሃነም ቅጣት መፍራትና ሞትን አብዝቶ ማስታወስ
16) …
አላህ…የተጋረጠብንን ፈተና በድል የምንወጣው ያድርገን! አሜን።