እንቅስቃሴ ይቁም በሚለው የኡስታዝ ሐሰን ታጁ ስነድ ላይ የቀረበ አጭር ምልከታ

 በአላህ ስም እጂግ አዛኝና ርህሩህ በሆነው

እንቅስቃሴ ይቁም በሚለው የኡስታዝ ሐሰን ታጁ ስነድ ላይ የቀረበ አጭር ምልከታ

አብዬ ያሲን ኢብራሂም

አፐሪ062013  |||  abyassin@yahoo.com

*****

ዑማው መንታ መንገድ ላይ እንደሆነ በመግለጽ የቱን አቅጣጫ መከተል አለብን በሚል ነጥብ ላይ የሚሽከረከር የመወያያ ሰነድ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ቀርቦ ሰሞኑን በመሰራጨት ላይ ይገኛል። ሰነዱ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሁለት ጎራዎች (እንቅስቃሴው ይቀጥልና መቆም አለበት የሚሉ) እንዳሉ በማሳየት ሁለቱም ለያዟቸው አቋሞች በዋቢነት በሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ላይ ቅኝትን ያደርጋል። በዚህ ሂደትም ኡስታዙ መከተል አለብን (እንቅስቃሴው መቆም አለበት) የሚለውን ሀሳብ በመደገፍ ከዚያ በተቃራኒው የሚቀርቡትን (እንቅስቃሴው መቀጠል አለበት በማለት) ሀሳቦች ውድቅ ያደርጋል። በመጨረሻም እንቅስቃሴው ከቆመ በኋላ የመንፈሳዊ ተሀድሶን መሠረት በማድረግ የተሻለ ሥራ መስራት እንዳለብን ያሳስባል።

የትግሉ ሂደት እንዲቆም ለማሣመን የሚሞክረው ሰነድ በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ላይ የተንጠለጠለ ነው። (1) ጎጂ ክስተቶችን ለመከላከል ያስችላል (ደም ከመፍሰስ፣ የእስልምና ገጽታ ከመበላሸት፣ የፓለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን፣ ወዘተ) የሚለውን በአንድ ጎን ሲያቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ (2) እንቅስቃሴውን በማቆም በሚመጣው እድል (የታሰሩ መሪዎቻችንን በማስፈታት፣ የዳዕዋ ስራን በማስቀጠል፣ ወዘት) ተጠቃሚዎች እንሆናለን የሚሉትን ያቀርባል። እነዚህ ሁለት የመከራከሪያ ሀሳቦች የየራሳቸው ጉድለት ያለባቸው ሲሆን ለአብነት የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል።

በመጀመሪያ የምንገነዘበው ሁለቱም ሀሳቦች እንቅስቃሴው ከቆመ መሻሻል ይመጣል ከሚል ግምት (assumption) ላይ ያረፉ ናቸው። ሁኔታዎች ከተሻሻሉ ደግሞ ጎጂ ክስተቶችን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ሁኔታው በሚፈጥረው አመች ሁኔታ በመጠቀም ገንቢና ጠቃሚ ስራዎችን መስራት እንችላለን ይለናል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ደግሞ የሚከብደው ሰላሙ እንጂ ጠቡ አይደለምና የተቃዉሞ እንቅስቃሴያችንን በፈለግነው ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ማስቀጠል እንደምንችል ይመክራል። ይህ አቀራረብ በርካታ መሰረታዊ ነጥቦችን ዘንግቷል።

ወደዚህ እንቅስቃሴው ሙስሊሙ የገባው መንግስት በወሰደው ትንኮሳ እና የመብት ረገጣ ተገዶ እንጂ ፈልጎት አይደለም። መንግስት ደግሞ የወሰደውን እርምጃ ሲወስድ እንዳው በአጋጣሚ ሳይሆን የራሱን የፓለቲካ ጥቅም አስልቶና አጥንቶ ሊሆን እንደሚችል ቢያንስ መገመት እንችላለን። ለእዚህ በመረጃነት አለም አቀፋዊ፣ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና ከዚያም ወረድ በማለት የገዥው ፓርቲ የፓለቲካ አይዶሎጅ አንስተን እያንዳንዳቸው ሊኖራቸው የሚችለውን ተፅዕኖ ማየት ይቻላል። ሆኖም ግን ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ መግባት ለእዚህ ፅሁፍ አስፈላጊ ባለመሆኑ እንዳለ እዘልለዋለሁ። ላሰምርበት የምፈልገው ግን ሙስሊሙ ተቃውሞውን በማቆሙ መንግስት ከመጀመሪያው አስቦ የተነሳበትን አላማ ከመተግበር መታቀብ ይቅርና ሂደቱ አለዝቦ ሊሄድ ይችላል የሚል እይታን ልናስተናግድበት የምንችለው ሁኔታ እንኳን የለም። እዚህ ላይ ምናልባት መንግስት ከወትሮውም አስቦ የተነሳው ነገር የለም። በድንገት የገባበት ነው የሚሉን ካሉ አንድን የመንግስት ፓሊሲ እንዲወጣ የሚረዱ አለም አቀፋዊና ሃገራዊ እንዲሁም መዋቅራዊና ግለሰባዊ ምክንያቶችን ካለማወቅ የሚመነጭ ነው ብለን ማለፉ ይቀላል። የመንግስት የረጂም ጊዜ እቅድ መሆኑን አስረጅ ካስፈለገ ደግሞ ዶ/ር ሽፈራው በግዮን ሆቴል ከአህባሹ አለቃ ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠው ይህንኑ በማስመልከት የተናገሩትን መለስ ብለን እንድንጎበኝ እጋብዛለለሁ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ባባለፉት የኢህዓደግ ሁለት አስርት የስልጣን ዘመናት ዉስጥ ያስተናገዳቸውን የመብት ረገጣዎች ዞር ብሎ ማስታወስም ተገቢ ነው።

ከዚሁ ጋር ተይያዞ ሊነሳ የሚገባው መንግስት በሙስሊሙ ላይ እያደረገ ላለው የመብት ረገጣ ምላሽ እያረፍን እንቀጥል የሚል ስትራቴጅን መከተል የማይቻል መሆኑን ነው። እንቅስቃሴው አንድ ጊዜ ከቆመ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ዳግም እንደማይነሳ እርገጠኛ እስከሚሆን ድረስ መንግስት እስራቱን፣ ግድያዉን አጠናክሮ ይቀጥልበታል እንጁ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። በአሁኑ ሰዓት እንቅስቃሴው ይቁም እና ሌለኛውን መንገድ እንሞክር ካልሆነ እንደገና ተመልሰን እንቅስቃሴያችንን እናስቀጥላለን የሚለው እይታ መንግስታት ጠላቶቸ የሚሏቸውን በምን መልኩ እንደሚታገሏቸው በጥልቀት ካለመረዳት የመነጨ እይታ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።

እንዳው ለውይይት ብለን የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ከቆመ በኋላ መንግስት አሁን እየሄደበት ያለውን አረመኔያዊና ኢፍትሀዊ ሂደት አስተካከለ ብንል እንኳን ይህ በራሱ የእንቅስቃሴው ትሩፋት እንጅ እንቅስቃሴው በመቆሙ የተገኘ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። መንግስት ከእንግዲህ በህዝቦች መብት ላይ መረማመድ እንደማይችል ትምህርት ሰጥቶ የሚያልፍ ይሆናል። የተቃውሞው ጥንካሬ መንግስት እየሄደበት ካለው የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲመለስ አስገዳጅ ሀይል ነበር ማለት ነው። ምንም እንኳን በኡስታዝ ሐሰን የተቃኘው ትንበያ ቢሳካ በዚህ ረገድ ይህ እንቅስቃሴ ያስገነኘው ፋይዳ እውቅና ሊቸረው ይገባል።

በቅርቡ በሰፊው እንዲሰራጭ ከተደረገው ሰነድ በፊት 11 ገጽ ያለው ተመሳሳይ ሰነድ ተሰራጭቶ አንብበናል። ቀደም ብሎ በተሰራጨው በዚህ ሰነድ ላይ እንቅስቃሴው ያስገኛቸው ውጤቶች አልተጠቀሱም። ተሻሽሎ የቀረበው ሰነድ ግን ጥልቀት ባለው መልኩ ባይሆንም እንቅስቃሴው አስገኝቷል ያላቸውን ትሩፋቶች ዘርዝሯል። በአቀራረባቸው ግን እንቅስቃሴው ይቁም የሚለውን ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማግባባትና ለመሸንገል ያሰበ መልክ አላቸው። የሙስሊሙ እንቅስቃሴም ጠባብና ወገንተኝነትን እንዲላበስ ሲደረግ በሀገር እና በህዝብ ደረጃ እየጣለ ያለው እምርታ ገሸሽ ተደርጓል። ለዚህም ሲባል ይመስላል የእንቅስቃሴው ድሎች ከሶስቱ ጥያቄዎች እይታ ብቻ እንዲቃኙ ተደርጓል። በቅድሚያ ተጠቃሽ ሊሆኑ ይገባቸው ከነበሩና ሀገራዊም ታሪካውም ፋይዳን ከሚያመላክቱ ድሎች መካከል ለምሳሌ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

 1. ጎጠኝነትን እና የአንድን አስተሳሰብ/አመለካከት ለተሻገረ የሙስሊም አንድነት መሰረትን ጥሏል። ይህ ድል በተለይ ለዘመናት በበርካታ ምሁራን እና ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሲተች የነበረውን ቡድንተኝነትን ላለፈ አንድነት እንዲሁም በብሄር ሳጥን ዉስጥ ተውጦ የመቅረትን አደጋ የሰበረና ለሀገር አቀፍ እስላማዊ ንቃተ ህሌና መዳበር መሰረት የጣለ ድንቅ ተሞክሮ ሆኗል።

 1. የፍርሀትን ልጓም ትውልዱ እንዲበጣጥስ ረድቷል።1987 በአንዋር መስጊድ የኢህዓደግ መንግስት ያደረገውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ያንንም በማስከተል በሙስሊሙ መሪዎችና ድርጅቶች ላይ የወሰደውን እርምጃ ሁላችንም የምናስታውሰው ብቻ ሳይሆን ያለፍንበትም ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አንገታቸውን ቀጥ ለማድረግ የሞከሩትን ሁሉ በመኮርኮም ሙስሊሙ ህብረተሰብ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንዲገባና ህይወቱን በፍርሀትና በጭንቀት እንዲገፋ መገደዱን ብዙዎች ይስማሙበታል፤ የሰነዱ አዘጋጅ ሳይቀር። በፓለቲካውም ረገድ ያየን እንደሆነ ምርጫ 1997ተከትሎ መንግስት የወሰደው እርምጃ ከዚያም የፓለቲካ ምህዳሩን በማጥበብና ከነአካቴው በመዝጋት በተቀናቃኞቹ ላይ የሚወሰዳቸው እርምጃዎች ኢትዮጵያዊያን በፍርሀት ተሸብበው እንዲኖሩ ማድረጉ ማንም ሊክደው የሚችል ጉዳይ አይደለም። በተለይ ደግሞ በሰፊው የተተቸው የጸረሽብርተኝነት ህግ ጸድቆ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የመብት ጥያቄን አንስቶ ዋጋ ሳይከፍል የሚተው ሰው እንደማይኖር ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው። በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት ህብረተሰባችን የፍርሀትን ሻማ አሽቀንጥሮ በመጣል ለመብቴ መከበር ራሴን እሰዋለሁ፣ የምገድልበት ምክንያት ባይኖረኝም የምሞትለት አላማ ግን አለኝየሚል ትውልድን አፍርቷል።

 1. የሀይማኖት ነጻነት እና የእኩልነት ጥያቄን በኢትዮጵያ የፓለቲካ ምህዳር ውስጥ ማስገባት ችሏል። ብሄራዊ/ሀገራዊ እና ብሄርተኛ የኢትዮጵያ የፓለቲካ አራማጆች የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ያነሳቸውን የእምነት መከበር ጥያቄዎች በማስመልከት መግለጫዎችን አውጥተዋል። ይህ በሰነዱ ላይ እንደመለከተው የሙስሊሙን ጥያቄ የፓለቲካ ድርጅቶች ለአላማቸው ማስፈጸሚያ እያደረጉ ነው ከሚለው ይልቅ ጥያቄው የፓለቲካ ድርጅቶችን ትኩረት በመሳብ አቋማቸውን ከዚያው አንጻር እንዲቃኙ አድርጓል ማለቱ ይበልጥ ተገቢነት አለው። ከአሁን በኋላ የሀይማኖት ጥያቄን ሳያካትት እና በአግባቡ ምላሽ ሳይሰጥ የፓለቲካ ስርዓትን በኢትዮጵያ ዘርግቸ እንቀሳቀሳለሁ ማለት የሚታሰብ አይሆንም። ይህ ደግሞ ለሀገርና ለህዝብ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ጉልህ ድል ነው።

 1. አለም አቀፍ የሆኑ እና የማይጨበጡ ቲውሪዎችን ተከትሎ ከመጉተልተል ሀገራዊ የሆነ የአስተሳሰብ እና የትግበራ አስፈላጊነት አጠናክረን የምንዘረጋበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ምንም እንኳን መንግስት እንቅስቃሴውን ከውጭ ሀይሎች ጋር ትሥሥር እንዳለው በማመላከት እኛም በውጭ የምናያቸውና የምንሰማቸው አይነት ፍትጊያዎች ዉስጥ እንድንገባ ቢናፍቅም እንቅስቃሴው ግን ሀገራዊ ባህሪን ተላብሶ ራሱን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ብቻ አስተሳስሮ እንዲቀጥል ተደርጓል። ከዚያም ወረድ በማለት የእንቅስቃሴውን ሂደት ካየንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተላለፉ መርሀ ግብሮች አተገባበር ከአካባበው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተቃኝቶ የሚከናወን ነው። ቲንክ ግሎባ፣ አክት ሎካ የሚለው ትልቅ መርህ አዉቀነውም ይሁን ሳናውቀው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ እየሰረፀ እናገኛለን። ከሀሳብ ወርደን ተግባራዊነትን ስናይ ይህ ሂደት ትልቅ ስኬት ነው።

 1. በሙስሊሙ ህብተሰብ ዘንድ ሰፊ የፓለቲካ መነቃቃትን ፈጥሯል። በፓለቲካው ረድፍ ንቁ የሆኑ የሀይማኖት መሪዎችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህብረተሰባችንም የፓለቲካ ብስለትን እያመጣ ይገኛል። በዚህም ሀይማኖት እና መንግስት አይገናኙም የሚለውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተገን በማድረግ ሀይማኖተኞች ፓለቲካን ሊያውቁ፣ ሊሰሙና ሊናገሩ አይችሉም የሚል እንድምታ ያለውን የኢህአደግ የሁለት አስርተ አመታት ድስኩር ማስቀረት እየተቻለ ነው።

 1. ከዚህ በፊት የሙስሊሙን የእምነት ተሀድሶ እንደ አደገኛ ሂደት ይመለከቱ ከነበሩ አካላት ላይ ሳይቀር እንቅስቃሴው ተጸዕኖውን ማሳደር ችሏል። በታሪካችን አይተነውና ሰምተነው በማናውቀው መልኩ ሙስሊም ያልሆኑ የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ከሙስሊም ወገኖቻቸው ጋር በራስ ተነሳሽነት ቆመው ማየት ከእንግዲህ ለኢትዮጵያዊያን ድንቅ ነገር አይደለም።

 1. በራስ መተማመንን፣ በራስ መመካትን እና የራስን እጣ ፈንታ ወሳኞች እኛው መሆናችንን እያስተማረን ነው።የሙስሊሙ ህበረተሰብ ያሳለፈው የስቃይና የመከራ ህይዎት የኢትዮጳያዊነትን ስሜቱ በእጅጉ እንደጎዳው ሁላችንም የምንስማማበት ነው። በአገራችን ጉዳይ ላይ መሳተፍ ይቅርና እኛን ብቻ በሚመለክቱ ጉዳዮች ላይ እንኳን ቆርጠን የመሳተፍ ዝንባሌ አይታይብንም። በዚህ እንቅስቃሴ የምናየው ግን ይህ ሁኔታ መቀየሩን ነው። ሙስሊሙ በልበ ሙሉነት እና በራስ የመተማመንና የመብቃቃት ስሜት መብቱን የማስከበር እንቅስቃሴውን እያደረግ ይገኛል። እጣ ፈንታችንን መወሰንም የእኛው ድርሻ እንጅ የሌላ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ችለናል። ለድክመታችንም ሆነ ለጥንካሬያችን ሌሎችን እንደ ሰበብ ከማቅረብና የጥገኝነትን ስሜት ከማስተናገድ እየራቅን መጥተናል። ሙስሊሙ የራሱን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ማንኛውም ድርጊት ጉልህ አስተዋጾ የማድረግ (አመራርን ከመሰጠት ጀምሮ) ብቃቱን በዚህ እንቅስቃሴ አማካይነት ከሀገር አልፎ በአለም ደረጃ ለሚሰማና ለሚያይ ሁሉ እያስተጋባ ይገኛል።

 1. መንግስት የሚወስዳችውን ኢፍትሀዊ እርምጃዎችን ሰላማዊ፣ አስተማማኛ እና ቀጣይነት ባለው እንደዚሁም ሰፊውን ህብረተሰብ ባማከለ መልኩ መቃወም እንደሚቻል እያስመሰከረ ይገኛል። ይህ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ሳይቀር በትምህርትን ሰጭነቱ ተጠቃሽ ነው። አለም አቀፍ እውቅናን የተቸሩ ተንታኞች ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ያለ ሀቅ ነው።

 1. የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ጠባብ የእምነትና የዘር ገደብ የጣሱ መሪዎችን፣ የመብት አቀንቃኞችን እና ምሁራንን ማፍራት ችሏል። ሰነዱ የመብት ጥያቄውን እንቅስቃሴ በሁለት ጎራ የተከፈለ አድርጎ ገና ከመጀመሪያው ሊያቀርብ ይሞክራል ወጣቱን በአንድ በኩል ዓሊሞችን፣ ምሁራንን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በሌላ ወገን በማስቀመጥ። እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ ተቃራኒ ነው። ይህ እንቅስቃሴ በአንድ ወይም በሌላው የህብረተሰብ ክፍል እየተካሄደ ያለ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እንቅስቃሴና ውሳኔ ነው። ለዚህ ደግሞ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እድሜ፣ የትምህርት ደረጃና የስራ ዘርፍ በመካከሉ ሳይገባ መሪዎችን እና ተከታዮችን ማፍራት በመቻሉ እንጂ በሌላ ተአምራዊ ምክንያት አይደልም።

 1. ሙስሊሙ ተቋማት አስራርና አደረጃጀትን በተመለከተ የተሀድሶ እንቅስቃሴዎች ገፍተው እንዲመጡ ሰበብ ሆኗል። መጅሊስን በተመለከተ በዶ/ር ኢድሪስ እየቀረቡ ያሉ የተሀድሶ ጥሪዎችና ጥረቶች ምናልባትም ይህ እንቅስቃሴ ባይኖር ኖሮ እናያቸው ነበር ብሎ መገመት ራሱ ከባድ ነው።

 1. ለሙስሊሙ ህብረተሰብ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ለይቶ የማውጣትን ልምድ እየቸረው ይገኛል። ለመንግስት ከቀረቡ ሶስት ጥያቄዎች ተነስተን እንቅስቃሴው እየተጓዘበት ያለውን ጎዳና ካየን እንቅስቃሴው የግልና የቡድን ፋላጎቶችን ወደጎን በማለት የወል ፋላጎቶች ጎልተው እንዲወጡ፣ ትኩረታችንም በእርሱ ላይ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል። ለመንግስት የቀረቡ ሶስት ወይም አራት ጥያቄዎችም ያላቸውን እምርታ በዚህ መልኩ ከቃኘነው እንቅስቃሴው ሙስሊሙ ህብረተሰብ በኢህአደግ መንግስት እይታ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ያለውን ቦታ ማስተካከልና ከተገቢው ቦታ እንዲቀመጥ የሚያስችል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ አይነት የአስተሳሰብና የእይታ ደረጃ በዚህ እንቅስቃሴ ሰበብ ባይሆን ኖሮ ልንደርስበት ብንችል እንኳን የበርካታ አስርት አመታትን ጥረት የሚጠይቀን በሆነ ነበር።

ለውይይት የቀረበው ሰነድ የደረደራቸው ድሎች እውነታ ያላቸው ቢሆንም ከላይ ለማስፈር ከተሞከሩትና በሰነዱ ላይ ሊካተቱ ከሚገባቸው ነጥቦች ጋር አያይዘን ስናይ እንቅስቃሴው ያስገኘውን እምርታ ሰነዱ አኮስሶ የሚያቀርብ ሆኖ እናገኝዋለን። በመሆኑም የእንቅስቃሴው መቀጠል ካለው ፋይዳ የሚያስከትለው ጉዳት ስለሚያመዝን ቢቆም ይሻላል የሚልን ሀሳብ እንዲቀበሉ አንባቢያንን የሚያባብል ይሆናል።

ሌላው ሰነዱ በእጅጉ የዘነጋው ነጥብ የቀረበው እንቅስቃሴያችንን እናቁም የሚለው ሀሳብ ሊተገበር ቢችል እንኳ በሙስሊሙ መካከል ሊፈጥር የሚችለው የመከፋፈል አደጋ ነው። ይህ እንግዲህ ሰነዱ እንዲሰራጭ ከተደረገበት መንገድ ጋር ተያይዞ ሲታይ የአዘጋጆችንና ሰነዱን ለማሰራጨት ተፍ ተፍ የሚሉ ወንድሞችን ሀላፊነት የጎደለው ሂደት እንገነዘባለን። በሙስሊሙ መካከል ወጥ የሆነ አስተሳሰብ ሰፍኖና ስምምነት ተፈጥሮ አንድ መንገድ እንድንከተል ከመጋበዝ ይልቅ ጥረታቸውን ሙስሊሙን የመከፋፈል አደጋ ስር እንዲሰድ አስቦ የተነሳ ያስመስለዋል። በተለይ እንቅስቃሴው ከደረሰበት ደረጃ በመነሳት የቀረበው አስተሳሰብ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ማግኘት ካልተቻለ የቀረው አማራጭ ሀይል ብቻ ነው ብለው ሊያምኑ የሚችሉ ቡድኖች ህልውና እንዲያገኙ መንገድ ከፋች ነው። በዚህም ሰነዱ አስወግደዋለሁ ብሎ ያሰበውን ሁኔታ ሳይሆን የሚወልደው ተቃራኒውን ነው።

እንቅስቃሴው ከቀጠለ የእስልምና ገጽታ ይበላሻል የሚለው ሌላው መሰረቱን የሳተ እይታ ነው። መንስዔን እና ውጤትን (ኮዝ ኤንድ ኢፌክት) ያጣረዘም ነው። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ይህን ሂደት የጀመረው መንግስት ነው። እንቅስቃሴው ቢቆም እንኳን መንግስት ከጀመረው እስልምናን እና ሙስሊሞችን ከማጠልሸት ተግባሩ፤ ለሰርዓቴም መሰናክል ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸውን ሁሉ ከማስወገድ፣ ከማሰቃየትና ከማዋረድ ይገታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይህ አይነቱ ሂደት ማናልባትም ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል የሚችል ነው ብሎ መገመት አግባብነት ይኖረዋል። መንግስት በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው የበላይነትን ለመያዝ እንደዚሁም አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ቁርጠኝነቱን እና ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ሲል ጸረኢስላም ጸረሙስሊም ፕሮፓጋንዳው በአጭሩና በቀላሉ ይገታል ተብሎ አይታሰብም።

የእንቅስቃሴው መቀጠል የእስልምናን ገጽታ ያደበዝዛል የሚለው እንቅስቃሴው በሂደቱ ካስመሰከረው ባህሪው ተገላቢጦሽም ነው። በዚህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሰላም አፍቃሪነታቸውን፤ እየተገደሉ፣ እየታሰሩና እየተደበደቡ ሳይቀር ከዚህ መርሀቸው ፍንክች የማይሉ፣ ለስርዓት ተግዥነታቸውን እና ጨዋነታቸውንም አስመስክረውበታል። የመንግስትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ አምክነዋል። ይህ ባይሆን ኖሮ ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያንን አዳርሶ በአለም አቀፍ ደረጃ ችግራቸው፣ በደላቸው ሊታወቅላቸው ባልቻለም ነበር።

ከላይ ከተነሱት በተጓዳኝ በሰነዱ ላይ የሚከተሉትን ጉድለቶችን እናያለን።

መንግስት ሊነካ/ሊደፈር የሚችል አይደለም በሚል እምነት ላይ የተመሰረተ ነው። የመከራከሪያ ነጥቦች ማሳረጊያ ተደርጎ የቀረበው የኸው እምነት ነው። ሰነዱ መንግስት በምንም መልኩ እጂ ሊሰጥ የሚችል እንደማይሆን እንዳውም እልክ ውስጥ ይበልጥ ገብቶ ጭጭ ያደርገናል የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ነው። እንቅስቃሴው በመንግስት ላይ ምንም አይነት ጫና ሊፈጥር የሚችል አይደለም የሚል ሀሳብም በሰፊው ተንጸባርቆበታል። ይህ ሽንፈትን እጣ ፈንታው አድርጎ የሚያይ ሰነድ እንቅቃሴው እስካሁን በመንግስት ላይ ያደረሳቸው ሽንፈቶችን እና ሀፍረቶች ሊያይ አይፈልግም። ይህ እንቅስቃሴ መንግስት ገና ከማለዳው ጀምሮ የሚያስተጋባውን እና የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ከሽብረተኝነት ጋር ለማያያዝ የሚጥረውን ፕሮፓጋንዳ ውድቅ እያደረገ ይገኛል። በሰነዱ ላይ በትክክል እንደተቀመጠው የአህባሽን አስተምህሮት በሃይል የመጫን እንቅስቃሴ አከርካሪው ተመትቷል። ይህ እንቅስቃሴ የኢህአደግ መንግስት የሚታወቅበትን ተቃውሞን በሃይል የማስተናገድ አቅሙን አሳጥቶታል። እንቅስቃሴው በእርግጥም በመንግስት ላይ ጫና ማሳደር እንደሚቻል ማሳየት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የበለጥ ጫና ማሳደር የሚችል አቅምም እንዳለው ያሳያል። እንቅስቃሴው ሙስሊምና ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን እንዲረዳዱና እንዲቀራረቡ ማስቻሉን ስናይ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ አጠቃላይ የፓለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን ተጽኖ ሊፈጥር የሚችል ነው።

ሌላው ስነዱ ይዞ የቀረበው የተሳሳት አመለካክት አደጋ ሊወገድ አይችልም የሚል ነው። ምንም እንኳ ይከሰታሉ የተባሉት አደጋዎች የመከሰት እድል የሚኖራቸው ቢሆንም እንቅስቃሴው እስካልቆመ ድረስ ሊወገዱ አይችሉም የሚለው ግን መሰረት የለሽ እይታ ነው። የሙስሊሙ እንቅስቃሴ እጀግ አስደማሚ የሆኑ የሰላማዊ ተቃውሞ ዘዴዎችን እየተገበረ ተጉዟል። በዚህም የተለያዩ አደጋዎችን አምክኗል። ሰነዱ እንደሚለው በመንግስት ሆደ ሰፊነት ሳይሆን እንቅስቃሴው ለመንግስት ሰበብ የሚሆኑ ሂደቶችን ሁሉ በማስወገድ በተለያየ ጊዜ ሊከሰቱ ይችላሉ የተባሉ ፍጥጫዎችን አስቀርቷል።

የቀረቡ የመፍትሄ ሀሳቦችም ይሁኑ እንቅስቃሴው ከቆመ ሊሰሩ ይችላሉ ተብለው የተቀመጡ ነጥቦች እውነታን ያላገናዘቡ እና በምኞት ደረጃ ብቻ ሊታዮ የሚችሉ ናቸው። የትኛው አካል ነው መንግስት እነዚህን ስራዎች እንዳያግድ የሚቆጣጠረው? እነዚህን መልካም ሂደቶችን ሙስሊሙ እንደሚያገኝ የሚያመላክተውስ የትኛው ሂደት ነው?

የስነዱ ትልቅ ድክመት የመሪዎችን ከእስር መለቀቀ እንደ ፓኬጅ አድርጎ አንኳን አያቀርብም። ህብረተሰቡ ህጋዊ ተወካዮቹ እስር ላይ ሆነው የትኛው ታማኝ ሰው ወጥቶ ነው እንቅስቃሴውን እንዲቆም ጥሪ የሚያቀርበው? እንቅስቃሴው ከቆመስ በኋላ ማን ነው መንግስትን ታሳሪዎችን እንዲለቅ የሚያደርገው? ይህን ጉዳይ በተመለከት የቅንጂት መሪዎች እንደ ምሳሌ ቀርበዋል። ለመሆኑ የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ምን ገጠማቸው? ይህን በግል ህይወታቸውም ይሁን አላማችን ብለው ሲንቀሳቀሱ ከነበረው የፓለቲካ አጀንዳቸው ልናየው እንችላለን። ለራሳቸውም ሆነ ለቆሙለት አላማ መካን እንዲሆኑ አልተደረጉምን? የሙስሊሙን መሪዎችና የቆሙለትን አላማ ተመሳሳይ እጣ እንዲገጥማቸው መስራት ይቅርና ማሰቡ በራሱ ዘግናኝ ነው።

ይህ አሁን ህዝብ እንዲወያይበት ተብሎ የተሰራጨው ስነድ ቀድም ብሎ በእስር ላይ ላሉ የሙስሊሙ መሪዎች ቀርቦ ውድቅ እንደተደረገ የሚገልጹ መረጃዎች ብቅ እያሉ ነው:: መሪዎችን ማሳመን ያልቻለን ሰነድ ወድ ህዝብ ይዞ ብቅ ማለት ለምን?

በመጨረሻም የመወያያ ሰነዱ ሙሉ ጥረቱን ያደረገው ሙስሊሙ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም በማሽበልበል ላይ ነው። ይህ ሲሆን ግን ሌለኛው አካል ሊወስድ ስለሚገባው እርምጃ የሚያቀርበው አንዳችም ነገር የለም። መንግስት በመስሊሙ ላይ እያደረገ ያለውን ወከባ እንዲያቆም እንኳን አይጠይቅም። በአገሪቱ እስር ቤቶች ውስጥ ፍዳቸውን እያዩ ያሉ ንጹሀን ዜጎችን እንዲለቀቁ መጠየቅስ?

ማጠቃለያ

ለውይይት የቀረበው ሰነድ በአጠቃላይ ሲታይ በፍርሀት የተሸበበ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ከግምት ሳያስገባ መሰረተ ቢስ የሆኑ ምኞቶችን ለመጋት የሚሞክር ነው። መንግስት የወሰደውን እና እየወሰደ ባለው የመብት አፈና ላይ አንዲትንም ሂስ ሳይሰነዝር በተቃራኒው የመንግስት አረመኔያዊ እርምጃ ሰለባ የሆነውን ንጹሀን ሙስሊም የመብት ጠያቂ ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራል። ወደፊትም መንግስት አሁን እያደረገ ባለው ኢፍተሀዊነት ቀጥሎ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ዴም የሚያፈሱ፣ ንብረት የሚያወድሙ እርምጃዎችን ቢወስድ ተጠያቂው ሙስሊሙ ህብረተሰብ እንደሆነ የቅድሚያ ፍርዱን ያሰፍራል። ጠለቅ ብለን ካየነውም መንግስት ይህን እንቅስቃሴ ማቆም እንዲችል አረመኔያዊ ፊቱን በሙስሊሙ ህብረተስብ ላይ እንዲያዞር የሚጋብዝ መልዕክትንም ተሸክሟል። የሙስሊሙን ዘላቂ ጥቅም አላፊ ለሆነው ለመንግስት ክብርና ማዕረግ አሳልፎ መስጠት የሚዳዳው ሰነድ ለሙስሊሙ ህብረተሰብም ሆነ ለሀገር የማይበጅ ነው። ሰነዱ የመወያያ ሰነድ ከመሆን ይልቅ እንቅስቃሴውን የሚፈርጅም ነው። ሙስሊሙ ህብረተሰብም ይህን ተረድቶ ሰነዱ ሊያስከትል የሚችለውን የመከፋፈልም ይሁን ሌላ አደጋ በማስወገድ አጠቃላይ ማንነቱ እና መብቱ እስከሚከበርድረስ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።