We are at a cross road – which one shall we follow?

Ustaz Hassen Taju released a 33 page paper proposing an end to the nearly two years of Ethiopian Muslims Movement. This will,  he urges, help us avoid the envitable harsh measure the government is likely to take if we continue with our movement while at the same time help us reap the fruits ending the movement will bring with it. Please follow this link to access the document.

In the mean time we would like share here with you one reactions  to this unexpected proposal that came from unexpected corner and at unexpected moment. We will publish selected reactions (pro and against) so as to help establish a balanced view of Muslims over the proposal.

ለማራቶኑ ፅሁፍ የተሰጠ የማራቶን ምላሽ

I. መግቢያ
ላለፉት ሀያ አመታት ገደማ በሀገራችን ለእስልምና እና ለሙስሊሞች ታላላቅ ስራዎችን ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል ሸህ ሐሰን ታጁን ግንባር ቀደም ብናደርጋቸው የሚያንሳቸው ቢሆን እንጂ አይበዛባቸውም ነገር ግን እኝህ ታላቅ ሰው ከሰሞኑ አንድ ፅሁፍ በስማቸው ተለቋል ምንም እንኳ ይህ ፅሑፍ ከእርሳቸው አእምሮ ይፈልቃል ብዬ ባልገምትም ግና ከእርሳቸው ጋር በጉዳዩ ላይ በተደረጉ ውይይቶች አቋማቸው በፅሁፉ ላይ ከተንፀባረቀው ሀሳብ ያልተለየ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። በመሆኑም ላለፉት 20 አመታት በርካታ ኢስላማዊ ስራዎችን የሰሩልን ሸህ እዚህ ነጥብ ላይ ተሳስተዋል ብዬ እንዳምን ተገድጃለሁ በመሆኑም ሸሁ ያነሷቸውን ነጥቦች አለፍ አለፍ እያልኩ በመቃኘት በዚህ ጉዳይ ላይ ያንፀባረቁትን አቋም በግሌ የማልቀበል መሆኔን ለማሳየት እሞክራለሁ።

የፅሁፌን ርዕስ “ሸህ ሀሰን ታጁ አንሰማዎትም” ስል የሰየምኩት ሸሁ ከዚህ ቀደም ያደረጉትን ኢስላማዊ እንቅስቃሴ በበጎ አይን የማይ መሆኔን ለማሳየት ሲሆን ግን ደግሞ በትግላችን ዙርያ አቋማቸውን እንደማልጋራ ለማሳወቅ ይበልጥ ይገልፅልኛል ብዬ ስላመንኩኝ ነው። “ለማራቶኑ ፅሁፍ የተሰጠ የማራቶን ምላሽ” የምትለዋ ሀረግ ደግሞ ምላሹ የጥናታዊ ፅሁፉን ያህል ባይሆን እንኳ በመጠኑም ቢሆን ረዘም ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።II. የፅሁፉ ጥቅላዊ ይዘት
ፅሁፉ በዋናነት የሙስሊሙን የተቃውሞ ሂደት ለማስቆም ታልሞ የተፃፈ ሲሆን በተለይም የጁምዓ ተቃውሞዎችን ለማስቆም የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል ፤ ዝርዝር ሀሳቦችን ቆየት ብዬ እመለስባቸዋለሁ። ሌላው በፅሁፉ ላይ የሚንፀባረቀው ሙስሊሙን ለሁለት መክፈል ሲሆን ተቃውሞው እንዲቀጥል የሚፈልጉና ተቃውሞው ይቁም የሚል ሀሳብ ያላቸው እንዳሉ ለማሳየት ጥረት ከመደረጉም በላይ ተቃውሞው ይቀጥል የሚሉት ወገኖች ብስለት የጎደላቸው፣ አፍለኝነታቸውን ያልጨረሱ ለጋ ወጣቶች እና በስሜት የሚነዱ ሰዎች መሆናቸውን ለማሳየት ሲሞከር በተቃራኒው ደግሞ እንቅስቃሴው እንዲቆም የሚፈልጉት በሳል፣ አዋቂ፣ ኡለሞች፣ ምሁራን እና የሐገር ሽማግሌዎች መሆናቸውን ለመጠቆም ተሞክሯል። የትግሉ አራማጆች ህፃናት እና ያልበሰሉ መሆናቸው በመታመኑም ይመስላል “አያ ጅቦ መጣላቹ” አይነት ማስፈራሪያዎችን ለመጠቀም ተሞክሯል።

የመብት ጥያቄዎቻችንን በተመለከተ ደግሞ ምንም እንኳ ምላሹን ባንቀበለውም የተመለሱ መሆናቸውን በመግለፅ ወደኋላ መመለስ እንደማይቻል ያስረዳል። ሌላው ደግሞ ሁሌም ቢሆን ለኮሚቴዎቹ ትእዛዝ እያደረና ለእነርሱም ያለውን ፍቅር በየጊዜው እየገለፀ ያለውን የመብት ታጋይ ኮሚቴዎቹ ላይ እንደጨከነና መታሰራቸውንም የሚፈልግ እንደሆነ ለመግለፅ የተሞከረበት አጋጣሚም አለ።
ከዚህ ውጭ ያሉት ሀሳቦች ብዙዎቻችንን የሚያስማሙ ሲሆኑ የስካሁኑ ትግል ያስገኛቸውን ድሎች እና አማራጭ የተባለውን መፍትሔ ለማስቀመጥ ተሞክሯል።

ጥቅላዊ ይዘቱን የማልቀበልባቸው ምክንያቶች

የመጀመሪያው ተቃውሞዬ የፅሁፉ አላማ ላይ የሚያነጣጥር ሲሆን ከላይ እንደገለፅኩት የፅሑፉ ዋነኛ አላማ ሰላማዊውን ተቃውሞ ማስቆም ነው። ተቃውሞው መቆሙ ምን ጥቅምን ያስገኛል የሚል ጥያቄ አንስተን ፅሁፉን በደንብ ከመረመርነው ደግሞ በተቃውሞው መቆም ሊገኝ የሚችለው ትልቁ ድል የኮሚቴዎቻችን መፈታት ሲሆን ነገር ግን ይህም ቢሆን የሚፈፀመው የመንግስት ክብር እና ግርማሞገስ እንደተጠበቀ ኮሚቴዎቻችን ጥፋተኛ ነን ብለው መንግስትን ይቅርታ ሲጠይቁ ነው።(እዚህ ጋር ከ97 ልምድ መውሰድ እንደሚቻለው ምናልባት ኮሚቴዎቻችን ሰላምን በሰበኩበት አንደበታቸው በአሩሲ አሳሳ፣ በገርባ፣ በሀረር እና በአዲስ አበባ ላይ መንግስት ለጨፈጨፋቸው ዜጎች እና ላወደመው ንብረት ተጠያቂዎቹ እኛ ነን ብለው መፈረም ሊጠበቅባቸው ይችላል።) ያም ሆነ ይህ እኛ በበኩላችን ኮሚቴዎቻችንን በደንብ ስለምናውቃቸውና ስለምንረዳቸው የተባለውን ፈፅመው እንኳ ቢፈቱልን ደስታችን ወደር አይገኝለትም ግና የነርሱ መፈታት እንዳለ ሆኖ ከተፈቱም በኋላ እንኳ በተለያዩ ክልልሎች የተነጠቅናቸው መሳጅዶቻችን፣ የተዘጉብን መድረሳዎችና የበጎ አድራጎት ተቋማት በዛው የሚቀጥሉ ከመሆኑም በላይ መንግጅሊሱ ተጨማሪ ነጠቃዎችን እና ጥቃቶችን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ለመፈፀም የሁኔታዎችን መረጋጋት አሰፍስፎ በመጠባበቅ ላይ መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ዝም በሉ እያለ ለተጨማሪ ጥቃት የሚያመቻቸንን ፅሁፍ እንቀበላለን ብሎ ማሰቡ እብደት ካልሆነ በስተቀር የሚታሰብ አይደለም።

ሌላው ፅሁፉን የማልቀበልበት ምክንያቴ ፅሁፉ ጥቅምና ጉዳትን አወዳድሮ ሐሳብ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሂስ መስጠት ሲገባው የሁለቱን ሐሳብ አራማጆች ለሁለት በመክፈል አንደኛውን አሞግሶ (ዑለማ፣ ምሁር እንዲሁም የሀገር ሽማግሌ እያለ) ሌላኛውን ለማንኳሰስ መጣሩ ከፕሮፌሽናል ፀሀፊ የማይጠበቅ ፅሁፍ እንዲሆን አድርጎታል። ደግሞም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለተመለከተ ሰው ተቃውሞው ይቁም የሚሉት በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች መሆናቸውንና ብዙሀኑ ዑለሞችን፣ ምሁራንን እና ሽማግሌዎችን ጨምሮ የትግል ሂደቱ እንዲቀጥል የሚሹ መሆናቸውን ለመገንዘብ ጊዜ አይፈጅበትም።

ሌላው ለጥያቄዎቻችን ተሰጠ የተባለውን ምላሽ እንኳን እኛ የመንግስት ባለስልጣናት ራሳቸው እንደማያምኑበት በራሳቸው አንደበት “ቢያንስ ቢያንስ የዓወሊያው ጥያቄያችን ተመልሷል አትሉምን???” በማለት አረጋግጠውታል። በመሆኑም መላሾቹ እንኳ እንዳልመለሱት የተረዱትን ጥያቄ እኛ ጠያቂዎቹ እንድንቀበለው መጠየቅ ምን ይሉት ቅዠት ነው???
ከዚህ ውጭ የመብት ታጋዮችን መሪዎቻቸውን እንደማይወዱና የመሪዎቹ መታሰር የሚያስደስታቸው አስመስሎ ማቅረብና ትግሉን የማቆምን ሀሳብ ለኮሚቴዎቹ ከማዘን ጋር ማስተሳሰር በሌሎች ሁለት ግለሰቦች ከዚህ በፊት ተሞክሮ ያልተሳካ ስትራቴጂ ነው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦችም “እኛ በርገር እየበላን ኮሚቴዎቻችን ታሰሩብን” እያሉ ለኮሚቴው ያዘኑ መስለው ለመቅረብ ጥረት አድርገዋል ግና አልተሳካላቸውም ።

ሌላውና የፅሁፉን ሚዛናዊነት የጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከተው ፀሀፊው ከኮሚቴዎቹ ጋር በሽምግልናው ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ የተሰጠውን ምላሽ ማስፈር አለመቻሉ ነው። የተለያዩ ወገኖችን እይታ እንዳስቀመጠ ሲያሰፍር ዋናዎቹን የትግሉ ፈርጦች በጉዳዩ ላይ ያሳዩትን አቋም ማንፀባረቅ አለመቻሉ ለምን??? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። የእነርሱን አቋም ለህዝብ ሳያሳውቁ በጎን ህዝቡን ጀንጅኖ ሀሳብ ለማስቀየር መሞከር ህዝቡን ከኮሚቴው ለመለየት የተደረገ ጥረት ስላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለን???

III. ዝርዝር ሀሳቦቹን የማልቀበልባቸው ምክንያቶች

ከላይ ያሰፈርኩት ጥቅል የፅሁፉን ይዘት ሲሆን እዚህ ክፍል ላይ ደግሞ አለፍ አለፍ እያልኩኝ ፅሁፉ ወዳነሳቸው አንኳር ነጥቦች በመጠቆም የማልቀበልበትን ምክንያት ላብራራ እሞክራለሁ።

ፅሁፉ ተቃውሞው መቀጠል አለበት የሚለውን መከራከሪያ ያየበት መነፅር
የተነሱት የመብት ጥያቄዎች በህይወት የሉም ይለናል ይህ ጥናታዊ ፅሁፍ፤ ከመጀመሪያው የመጅሊስ ምርጫ ጥያቄ ላይ በመንተራስም እንዲህ ሲል የሞተ ጥያቄ መሆኑን ለማብራራት ይሞክራል “…ምርጫው ተከናውኗል። በሂደቱ ላይ ያለን ቅሬታና አስተያየት እንዳለ ሆኖ ወደኋላ መመለስ ይቻላል ብዬ ግን አላምንም።… “ እዚህ ቦታ ላይ ፅሁፉ ለጥያቄያችን መሞት እንደምክንያት ያቀረበው የፀሀፊውን የግል አስተያየት ሲሆን ፀሀፊው ዳግም ምርጫ ማካሔድ አይቻልም ብሎ በማመኑ የተነሳ ያነገብነው ጥያቄ እንደ ሙት መቆጠር እንዳለበት ደምድሞ አልፏል። እኛ ደግሞ የተያያዝነው መንገድ የትግል መንገድ እንደመሆኑ መጠን አይቻሉም፣ አይታሰቡም፣ አይደፈሩም እንዲሁም አይሞከሩም የተባሉ መንገዶችን ሁሉ በሰላማዊ ትግላችን ደርምሰን እንደምንጥላቸው በአላህ ላይ ተስፋ አለን። የኛ እና የፅሁፉ ባለቤት ልዩነት ተስፋ መቁረጥ እና ተስፈኝነት ያመጣው ለውጥ ከመሆን በዘለለ ስለጥያቄያችን መሞት የሚያመላክተው ነገር የለውም። አምላካችን አላህ ደግሞ ሁሌም ቢሆን ተስፈኞች እንድንሆን እንጂ ተስፋ እንድንቆርጥ ስላላዘዘን በዚህ ረገድ እኛ ከፀሀፊው የተሻለ በአላህ ቃል ላይ የተደገፍን ነን። ይህ ተስፋችን ደግሞ ጥያቄያችን ላይ ህይወትን ይዘራል።

ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ሲዞር ደግሞ እንዲህ ይለናል “…አስተሳሰቡን (አህባሽን) በሀይል ለመጫን የሚደረገው ሙከራ ከእንግዲህ ሞቶ የተቀበረ ይመስለኛል። አዋጭ እንዳልሆነ ራሱ ሙከራውን ያደረገው ወገን እንደተገነዘበው ጥርጥር የለኝም። …“ አሁንም በድጋሚ ለጥያቄዎቻችን መሞት እንደምክንያት የቀረበው የፀሀፊው ግምት ሲሆን ይመስለኛል እና ጥርጥር የለኝም በሚሉ ቃላት ጥያቄዎቻችን ሙት መሆናቸው እየተነገረን ይገኛል። ይገርማል መሳጅዶቻችንን በጠመንጃ በተነጠቅንበትና ያልተቀማነውንም ለመቀማት አድብተው በተቀመጡበት በዚህ ሰዐት በሀይል መጫን ብሎ ነገር አክትሞለታል የሚል መከራከርያ ይዞ መነሳት እውን ፀሀፊው ሀገር ውስጥ አለን??? የሚል ጥያቄን ለዓፍታም ቢሆን ያጭራል። ይኸው ትናንት አይደል እንዴ ቢላል መስጅድን አስረክቡን ሲሉ መንግጅሊሶች ወደ ቢላል መስጅድ የተመሙት ይህ ሁሉ በሚሰማበት ሀገር ውስጥ ተቀምጦ ሀይል የለም ብሎ መሞገቱ የጤና ነውን???

የዓወሊያው ጥያቄያችንን ሙትነት ሲያብራራ ደግሞ እንዲህ ይላል “…ለዚህ ተቋም ሲባል ሀገሪቱ ከምትተዳደርባቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የሚገዛ ህግ የተለየ አዲስ አሰራር መንግስት እንዲፈጥር የምንጠብቅ ከሆነ ተሳስተናል።… “ እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ የአወሊያ በቦርድ ይተዳደር ጥያቄ ከህግ ውጭ እንደሆነ በመጥቀስ እርሱም እንደሌሎቹ ጥያቄዎች ሁሉ ሙት መሆኑን ሊያረዳን ይሞክራል። እሺ ይሁን በቦርድ መተዳደሩ ከህግ ውጭ ነው ቢባልም በመጅሊስ መተዳደሩ ግን የህግ ማእቀፍ እንዳለው በፅሑፉ ላይ ተወስቷል። ይህ ከሆነ ዘንዳ የዓወሊያው ጥያቄያችን በመጅሊስ ላይ ያነሳነው ጥያቄ በዓግባቡ ከመመለሱ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ይኖረዋል ማለት ነው፤ በዚህ አግባብ ደግሞ መጅሊስ ላይ ያሉ አመራሮች በሕዝቡ ይመረጡና አወሊያም ለሕዝባዊው መጅሊስ ይስጥ በማለት ጥያቄውን መስመር ማስያዝና ወደ ህግ ማእቀፍ ማስገባት ይቻላል ማለት ነው። በመሆኑም ሦስቱም ጥያቄዎቻችን ከፅሁፉ የተዛባና ሚዛኑን ያልጠበቀ እይታ ውጭ ህያዋን መሆናቸውን መናገር ይቻላል።

ሌላው በፅሁፉ ላይ የቀረበው አተያይ ኮሚቴዎቹን ማስፈቻ መንገድ ሲሆን ከ97 ልምድ በመነሳት አሁንም ቢሆን ኮሚቴዎቹ ሊፈቱ የሚችሉት በዛ መስመር ብቻ መሆኑን በመግለፅ ትግላችን አላስፈላጊ መሆኑን ያብራራል። ከታሪክም ልንማር እንደሚገባን እንዲህ ሲል ያስቀምጣል “…ያለፉት ክስተቶች ትምህርት ካልሆኑን ታሪክ ማጥናት ምን ይፈይዳል?…” አዎ ታሪክን የምናጠናው ካለፈው ለመማር መሆኑ አያጠያይቅም ግና ከታሪኩ ትምህርት ለመውሰድ ቢያንስ ቢያንስ ክስተቶቹ መመሳሰል ይጠበቅባቸዋል። የ97ቱ ግርግር የፖለቲካና የስልጣን ሽኩቻ አሁን የተያዘው ትግል ደግሞ መብትን የማስከበር ፤ የ97ቱ ትግል በተቀናጀ አመራር ያልተሰናዳ አሁን ያለው ትግል ደግሞ ታጋዮች እየተናበቡ የሚሄዱበት ፤ የ97ቱ ትግል ህዝቡ ግብ ሳይኖረውና የተመቻቸ የመረጃ ልውውጥ መድረክ በሌለበት ሁኔታ የተካሔደ አሁን ያለው ደግሞ ህብረተሰቡ ጥያቄዎቹን ከደሙ ጋር አዋህዶና የራሱን የመረጃ ኔትዎርክ ዘርግቶ የሚሳተፍበት። እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ባሏቸው ትግሎች መካከል በአንዱ ላይ የታየውን ሁነት ለዚህኛው እንደሚሰራ ማስቀመጡ አግባብነት የለውም። ቢያንስ ቢያንስ ከታሪክ ትምህርት መውሰድ እንኳ ቢያስፈልግ መወሰድ ያለበት ከመሰል ሀይማኖታዊ ትግሎች ነው እንጂ ለዱንያዊ ስልጣን ተብሎ የተደረጉ ትግሎች በፍፁም በአላህ መንገድ ላይ ለሚደረግ ትግል ትምህርት መውሰጃ ሊሆኑ አይገባም። የፖለቲካ ስልጣን ታጋዮች ቢሳካላቸው በመጠነኛ ግብግብም ቢሆን ስልጣን መያዝ ግባቸው ሊሆን ይችላል የዲን ታጋዮች ግን መብታቸውን ለማስከበር ከመታሰርም በላይ ህይወታቸውን አሳልፈው እስከመስጠት የሚያደርስ እምነት በውስጣቸው ይናኛል ስለዚህም ነው አሚራችን አህመዲን ጀበል “የምንገድልበት አላማ ባይኖረንም የምንሞትለት አላማ ግን ኢስላም አለን” ሲል የተናገረው። በመሆኑም መታሰራቸውም ሆነ ሌሎች በአላህ መንገድ ላይ ሲታገሉ የሚደርሱባቸው ስቃዮች ወንጀላቸውን ማራገፊያ እና ደረጃቸውን ከፍ ማድረጊያ ቢሆኑ እንጂ ሌላ አይደሉም። በመሆኑም ትምህርት መውሰድ እንኳ ቢያስፈልገን ከሌሎች ሀይማኖታዊ ትግሎች ትምህርት መውሰድ ይቻላል እንደ ምሳሌም ዛሬ ላይ ትልቅ ፓርቲ መሆን የቻለው የኢህዋነል ሙስሊሚንን ፓርቲ ብናነሳ ከዛሬ ስኬቱ በስተጀርባ ቀደምት መስራቾቹ ያሳዩት ፅናትና ህይወታቸውን አሳልፈው እስከመስጠት ድረስ የከፈሉት መስእዋትነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ትላንት እነዚያ መስራቾቹ ተልፈስፍሰው እስርን እና ሞትን ፈርተው የተቃዋሚዎቻቸውን ፍላጎት ተከትለው ቢጓዙ ኖሮ ዛሬ ላይ ኢህዋን የሚባል ፓርቲን ባልሰማን ነበር። ነገር ግን እነዚያ ታጋዮቹ በከፈሉት መስእዋትነት ከረዥም ጊዜ የትውልድ ቅብብሎሽ በኋላ ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ ለመጓዝ የሚረዳቸው መስመር ላይ እንዲያርፉ አስችሏቸዋል። ታድያ እንዲህ ካሉት የትእግስትና የፅናትን ውጤት ከሚያሳዩ ትግሎች ትምህርት መውሰድ ሲገባን ገና አንድ አመት ብቻ ከታገልን በኋላ “እኛ ተስፋ ቆርጠናልና እናንተም ተስፋ ቁረጡ” የሚል ይዘት ያለው ጉትጎታ ለህዝብ ማስነበቡ እንዴት አግባብ ይሆናል???

ፅሁፉ ካካተታቸው ሀሳቦች መካከል ከታጋዮች መካከል መንግስትን የመጣል አላማ ያነገቡ እንዳሉ ሲገልፅ ነገር ግን እነዚህ አካላት የዲያስፖራ ሰዎች መሆናቸውን ይገልፃል። በመሰረቱ ፅሑፉ ዋነኛ አላማው ሐገር ቤት ያሉትን ታጋዮች ትግላቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን በየሀገሩ የሚወራውን እንቶፈንቶ ወሬ ሰብስቦ ማስቀመጡ ጠቃሚነት አይኖረውም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እኛን የሚያስጨንቀን የመብታችን መከበር አለመከበር ጉዳይ እንጂ የዓንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ መቆየትና አለመቆየት አንገብጋቢው አጀንዳችን አይደለም።

አንዳንድ የፅሁፉ መከራከሪያዎች ፍፁም ብስለት የጎደላቸው ሲሆኑ በዚህ አንፃር ከቀረቡት መካከልም ከታጋዮች መካከል በየጁምዓው የሚደረገውን ተክቢራ እንደ እግርኳስ ትእይንት ለመዝናኛነት የሚጠቀሙበት እንዳሉ ለማሳየት መሞከሩ አንዱ ነው እንዲህ ሲልም ይገልፀዋል “…ይህ የየሳምንቱ ተቃውሞ ልክ እንደ ኳስ አይተንና ተደስተንበት የምናልፈው ጉዳይ አይደለም አንድ ቀን እሳተ ገሞራ ሆኖ ከነህይወታችን ሊቀብረን ይችላል።…“ ፅሁፉ ይህንን አገላለፅ የተጠቀመው ምናልባት ያልበሰልነውን፣ አፍለኞቹን ህፃናት ታጋዮችን ለማስፈራራት አልሞ ሊሆን ይችላል። ግና እኛም ብንሆን በአላህ መንገድ ላይ ብንገደል ማእረጋችን ነው እንጂ ውርደታችን እንዳልሆነ ልንገልፅ እንወዳለን።

አላማችን ከመንግስት ጋር መበሻሸቅ እንደሆነ ተደርጎ መቅረቡም ከፅሁፉ ጉድለቶች ውስጥ የሚቆጠር ነው ከዚህ ውጭ ሌሎች የትግላችንን አላማ የማይወክሉ ምክንያቶችም የተዘረዘሩ ሲሆን እኔ በበኩሌ ለተጠቀሱት አላማዎች የማልታገል በመሆኔ ሁሉም ላይ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቤያለሁ።

የትግላችን አላማ ህያው የሆኑት ቀላል ጥያቄዎቻችንን ማስመለስና ለነዚህ ቀላል ጥያቄዎች ሲባል በእንግልት ላይ ያሉ የኢስላም ፈርጥ አንበሶቻችን በክብር ተፈተው ለእነርሱ የሚገባቸውን የጀግና አቀባበል ማድረግ እንደሆነ አስምሬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ለዚህ አላማ ስታገል ደግሞ በአላህ ላይ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ትግሉ ከዓመት ዓመት ተሻገረ ብዬ ተስፋ አልቆርጥም በኔ እድሜ እንኳ ምላሽ ባያገኝ መብትን የማስከበር ትግልን ለቀጣዩ ትውልድ አውርሼ አልፋለሁ ኢንሻአላህ!!!! በመሆኑም በዚህ ኒያ ላይ ስታገል ተስፋ በመቁረጥ የተሸነፋቹ ካላቹ “እኛ ተሸንፈናልና አንተም ተሸነፍ” እንድትሉኝ አልሻም እርዳታም ከአላህ ብቻ እንጂ ከማንም አይደለም።

ትግሉን የማስቆም መነሻ እና ትንታኔው

በፅሁፉ የሰፈረው ሌላኛው ትንታኔ ደግሞ መቆም አለበት አሉ የተባሉ ግለሰቦችን መነሻና ትንታኔ ሲሆን እዚህ ክፍል ላይ ካለፈው በተለየ መልኩ ፅሑፉ ድጋፉን ሲቸራቸውና ስጋታቸው ተጨባጭ መሆኑን ለማሳየት ሲጥር ይስተዋላል። ይህንንም ክፍል እንዳለፈው ክፍል ሁሉ አለፍ አለፍ እያልኩ እቃኘዋለሁ።

ለተቃውሞው መቆም የመጀመሪያ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው የጥያቄዎቻችን ባሕርይ ውስንነት ሲሆን እንዲሕ ሲል ይተነትነዋል “…የቀረቡት ጥያቄዎች ጠያቂው ወገን በፈለገው ይዘትና ቅርፅ ሊመለስ ቢችል እንኳ የህዝበ ሙስሊሙ መሰረታዊ ችግሮችን የሚፈቱ አይደለም። በጥያቄዎቹ ላይ ቢያንስ ቢያንስ የዑለሞች እና የምሁራን ኢጅማእ የለም።…” ይህ ፍፁም የተሳሳተ ምልከታ ስለመሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ካነሳው ጥያቄ ውስጥ አንዱ እኮ ወኪል ድርጅቴ መጅሊስ ፈር ይያዝልኝ የሚል ነው። ይህ ድርጅት ህዝብ በሚመርጣቸው ኢስላምን ሊያገለግሉ በሚችሉ ግለሰቦች መያዙ በኢትዮጵያ ሙስሊም ላይ የሚኖረው ፋይዳ ትንሽ ነው ብሎ መገመቱ ፍፁም ከእውነት የራቀ ግምት ነው። ይህ ድርጅታችን ካለው ግዝፈትና አቅም ጋር ከብልሹ አሰራር ተላቆ ለህዝበ ሙስሊሙ ተመላሽ ቢደረግ ሊሰራቸው የሚችላቸውን ስራዎች የትኛውም አይነት ኢስላማዊ እንቅስቃሴ ሊተካው አይችልም።

ሁለተኛው የመከራከሪያ ነጥብ ፍፃሜው አሳዛኝ እንዳይሆን የሚል ሲሆን ፅሁፉ በሚከተለው መልኩ አቅርቦታል “…ተቃውሞው አላስፈላጊ ለሆነ ጊዜ መራዘሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚለው እምነት ፅድቅ የተቸረው ዕለት ሂደቱን በሀይል የመቆጣጠር እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። በሂደቱ ምናልባት ደም ከፈሰሰ ለማንኛችንም ወገን አይበጅም…” ስራዎቻችንን ለአላህ ብለን እስከሰራናቸው ድረስ አሳዛኝ የሚባል ፍፅሜ ሊኖረን አይችልም። እንዴ :- ሙስሊሞች ነን እኮ!!! በፅሁፉ ላይ እንደተንፀባረቀው ሰላምን ተላብሰን መብታችንን በመጠየቃችን የተነሳ የጥይት ቃታ ተመዞብን ህይወታችንን ብናጣ እንኳ ሸሂዶች ነን ፤ ሸሂድነት ደግሞ ጥቂቶች የሚታደሉት ወርቃማ እድል እንዲሁም ስኬታማ ፍፃሜ እንጂ አሳዛኝ ፍፃሜ ሊሆን አይችልም። በአላህ መንገድ ላይ ለዲናችን ከመታገል ምናባዊ ስጋት አያግደንም እኔ በበኩሌ መንግስት የሀይል እርምጃ ሊወስድ ይችላል ብዬ በጠረጠርኩባቸው ጁምዓዎች ላይ እንኳ ለሰበብ ያህል እንደ ሎሚ ጭማቂ ያሉ አስባቦችን ይዤ ተንቀሳቅሻለሁ እንጂ ገና ለገና እርምጃ ይወሰድብኛል ብዬ በፍርሀት ቤቴ አልተቀመጥኩም። እንደተባለው የሀይል እርምጃ ሰለባ እንኳ ብሆን የወንጀሌ ማበሻ የደረጃዬ ከፍ ማድረጊያ አጋጣሚ አድርጌ እቆጥረዋለሁ እንጂ እራሴን ለአላስፈላጊ ጉዳት እንደዳረኩ አይሰማኝም።

ሦስተኛው መከራከሪያ ነጥብ የኢትዮጵያ እስልምና ስዕል መጠልሸት የሚል ሲሆን ትግሉ የማይቆም ከሆነ መንግስት በሚሰራው የማጠልሸት ስራ የኢትዮጵያ እስልምና ስዕል ይጠለሻል የሚል አመክንዮን ያንፀባርቃል። በመሰረቱ ለኢትዮጵያ እስልምና ስዕል ትልቁን ቦታ የሚይዘው ወሳኙ ነጥብ የኛው የሙስሊሞች ባህሪ እንጂ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ መሰረታዊ ለውጥን አያመጣም ኢስላም በመንግስት ደረጃ ይንቋሸሽበት በነበረው የዐፄ ስርዓት ውስጥ እንኳ ህብረተሰቡ ሙስሊም ማለት ገንዘብ ሊቀመጥበት የሚገባ ከማጭበርበር እና ሌብነት የፀዳ ታማኝ የፈጣሪ ሰው መሆኑን ያምን ነበር ለዚህ እሳቤ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የወቅቱ ሙስሊሞች ያሳዩት ግብረገብነት ነው። እንጂማ ዐፄዎቹ ፍላጎታቸው ኢስላም የገሪባዎች እና ምንም የማያውቁ መሀይማን እምነት እንደሆነ ማስተማር ነበር ግና በሙስሊሙ ህብረተሰብ የተገራ ባህሪ ህዝቡ እውነቱን መገንዘብ ችሎ ነበር። አሁን ወዳለንበት ተጨባጭም ስንመጣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ትግሉን በሰለጠነ መንገድ እያካሔደ ባለበትና መብቱን በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀ ባለበት በዚህ ወቅት በመንግስት ሊነዛ የሚችለው ፕሮፖጋንዳ ሀቁን የመገልበጥ አቅም አይኖረውም። ደግሞም ይኸው ለአንድ አመት ያኽል መንግስት ፕሮፖጋንዳ ከመንዛት እኮ አልተቆጠበም ዳሩ ግን እኛ እያሳየን ያለነው የሰለጠነ አካሔድ መፈናፈኛ ሊሰጠው አልቻለም አልሀምዱሊላህ!!!።

አራተኛው መከራከሪያ ነጥቡ ትግሉ በቀጠለ ቁጥር ተጨማሪ እስርና ስደት ይኖራል ይህ ደግሞ ሊካካስ የማይችል ኪሳራ ነው ይለናል። ግና ትግሉን ማቆሙ ለዚህ ችግር መፍትሔን ባያመጣስ የሚለውን ጥያቄ ሲመልስ ከትግሉ መቆም በኋላ መንግስት እርምጃውን ይቀጥላል የሚለው “ጥርጣሬ” ብቻ ነው በትግሉ መኖር ምክንያት እየደረሰ ያለው እስር እና ስደት ግን “ተጨባጭ” ነው ሸሪዓችን ደግሞ ከጥርጣሬ ለተጨባጭ ቅድሚያን ይሰጣል <<ፊቅሁል አውለውያት>> በማለት ምላሽ ይሰጣል። በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች አንዱ ፅሁፉ ለውይይት የቀረበ ነው እየተባለ ግና ትግሉ መቆም አለበት የሚሉ ግለሰቦችን መከራከርያ በጠጣር መሰረት ላይ ለማኖር ሲጥር በተቃራኒው ወገን ያለውን የብዙሀኑን ህዝብ መከራከሪያ ደግሞ መሰረት ለማሳጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በዚህም የተነሳ ትግሉ ቢቆምም ባይቆምም መንግስት ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለመጨቆን እንደ እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰበት ያለውንና በአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ አስፍሮት ያለውን ፕላኑን ጥርጣሬ ነው እያለ እስኪ ትግሉን አቁመን ደግሞ እንሞክረው አይነት ምክርን ይለግሰናል ፤ ያሳዝናል!!!።

ፅሁፉ ተቃውሞውን የመቀጠል ሀሳብን ሲያጣጥል እንዲህ ይለናል “…መንግስት ሊበቀለን ስለሚችል ተቃውሞውን እንቀጥል የሚሉ ወገኖች ምን እያሉ መሰላቹ መንግስት እስከሚወድቅ ድረስ በየመስጂዱ እንጩህ እያሉ ነው። መንግስት እነርሱ እንዳሉት እስኪጣል ድረስ ምን ያህል አመታትን ይፈጃል? አይታወቅም። እስከዚያ ድረስ በተቃውሞው መቀጠል ያዋጣል? ይቻላል? መንግስት በሕገወጥነት የፈረጀውንና ሊጥለው ያለመውን እንቅስቃሴ እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ ታዛቢ ሀይል ሊሆን አይችልም።….“ ፅሁፉ ሀተታውን በመቀጠል መንግስት የሀይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያብራራል። በመሰረቱ መንግስት ትግላችንን ከጀመርን ጊዜ አንስቶ እኮ ተደጋጋሚ የሀይል እርምጃዎችን ወስዷል ግና ይህ እርምጃው አበረታን እንጂ አላሳነፈንም። ከዚህ በዘለለ መንግስትን ስለመጣል በፅሑፉ ውስጥ ተደጋግሞ የተነሳው ሀሳብ እኛ መሰረታዊ ጥያቄያችን መብታችንን ማስከበር ሆኖ ሳለ ለመብታችን መከበር የመንግስት ለውጥ የግድ ከሆነም ወደዛ የማንገባበት ምንም ምክንያት የለም የጊዜውን ጉዳይ በተመለከተ ከላይ እንደጠቀስኩት ምናልባትም መብትን የማስከበር ሂደቱ በትውልዶች ቅብብሎሽ የሚሳካ ሊሆን ይችላል ዋናው ነጥብ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል የሚለው ጉዳይ ሳይሆን መብቱን የሚጠይቅ ኩሩ ትውልድ እያፈሩ መሔዱ ላይ ነው።
አምስተኛው መከራከሪያ የትግሉ መቀጠል የታሳሪዎቹን በይቅርታ የመፈታት እድል ያጠባል የሚል ሲሆን ኮሚቴዎቻችን ፍርድ ከተበየነባቸው በኋላ ብቸኛው የመውጫ መንገድ የይቅርታ መንገድ መሆኑን በመግለፅ የትግሉ መቀጠል ይህንን በር እንደሚዘጋ ይተነትናል። እዚህ ቦታ ላይ ተጨማሪ አስተያየትን ለመስጠት የኮሚቴዎቻችንን ወቅታዊ አቋም እና ፍላጎት ማወቅ ግድ ይላል የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም ፅሑፉን ለውይይት ከሆነ ያቀረቡት በሽምግልናው ላይ ኮሚቴዎቹ ያሳዩትን አቋም በዝርዝር መግለፅ ይጠበቅበት ነበር። እኛ ኮሚቴዎቻችን በእስካሁኑ ሂደት ከበቂ በላይ መስእዋትነትን ከፍለዋል ሀላፊነታቸውንም ተወጥተዋል የሚል ፅኑ እምነት አለን ከዚህ በኋላ በትግላችን እንድንቀጥል ከፈለጉም አህለን ወመርሀበን ብለን እንቀበላቸዋለን በሽምግልና መውጣት ፈልገው ከሆነም መክፈል የሚገባቸውን መስዕዋትነት ስለከፈሉ ለሽምግልናው መሳካት የበኩላችንን እገዛ እናደርግላቸዋለን። ግና ይህ ማለት ምናልባት የአካሔድ ለውጥ ያስደርገን ይሆናል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ ለመብታችን መታገልን የህይወት ግባችን አድርገን ይዘነዋል።

በስድስተኛነት የተነሳው ነጥብ የመደበኛ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች መቆም ሲሆን ተቃውሞው ብዙ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ምክንያት መሆኑን ጠቅሶ የተቃውሞው መቆም ለነዚህ እንቅስቃሴዎች ማንሰራራት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። በመሰረቱ ብዙዎች እንቅስቃሴዎች ሊቆሙ የቻሉት መንግስት አቅዶ በወሰዳቸው የጣልቃ ገብነት እርምጃዎች እንጂ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞ የተነሳ አይደለም። ደግሞ እያንዳንዱ ኢስላማዊ እንቅስቃሴ ሙሀደራው፣ ዳእዋው፣ ኹጥባው፣ ኢማምነቱ ወዘተ ከመንግጅሊስ በሚሰጥ ፍቃድ ብቻ ሊሆን እንደሚገባው ተነግሮን እያለ ተቃውሞ ካቆምን ሁሉም ኢስላማዊ እንቅስቃሴ በተለመደው አኳኋን ይቀጥላል ብሎ መገመት እንዴት ይቻላል???
መከራከሪያ ቁጥር ሰባት ደግሞ እንዲህ ይነበባል “…የእስልምና ጠላቶችን አላማ ማሳካት: የእስልምና ጠላቶች አህባሽ፣ ሶፊ ወይንም ሰለፊ መሆናችን አይደለም የሚያሳስባቸው ። ለእስልምና ተቆርቋሪ የሆነ ትውልድ ከመንግስት ጋር በመላተም በግፍ ወደ እስር ቤት እንዲወርድ ፣ እንዲገደልና እንዲሰደድ እንጂ። ይህ ሲሆን የእስልምና እንቅስቃሴ ይስተጓገላል። ህዝባችን መምህራኖቹን ካጠገቡ ያጣል የእስልምና ጠላቶች አላማ በቀላሉ ይሳካል።….” ሁሉንም የፅሁፉ ክፍሎች ፍሬ በፍሬ እያነሳሁ የመተቸት አላማ የለኝም ግና የጠላቶቻችን ሴራ ስለታገልን እና ትግል ስላቆምን የሚለዋወጥ አይደለም ምናልባት ሁለት አመት ወደኋላ ብናስብ እኮ ሁሉም ሙስሊም ትግል የሚባል ነገር ሳይኖር በየቤቱ ቁጭ ያለበት ተጨባጭ ነበር ያለው፤ ግና ጠላቶቻችን ከማሴር አልቦዘኑም ዛሬም ወደትግሉ ያስገባን ዋነኛው ምክንያት እኮ የእነርሱው የቤት ስራ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በመሆኑም ትግሉ ቢቆም ጠላቶቻችን ምናልባት እኛን የሚየጠቁበትን ስልት ይቀይሩ እንደሆን እንጂ እኛን ከማጥቃት ወደኋላ አይሉም።

ስምንተኛው የመከራከሪያ ነጥብ ደግሞ “..ለአክራሪ አስፈፃሚ አካላት ሽፋን መስጠት…” ይለናል በዚህ የመከራከሪያ ነጥብ መነሾም በየትምሕርት ተቋሙ እና በተለያዩ ተቋማት አስፈፅሚ አካላት ሙስሊሙን ለመጨቆን ተቃውሞው ሽፋን እንደሚሰጣቸው ያትታል። እንደላይኛው መከራከሪያ ሁሉ እዚህም ጋር ፅሁፉ ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባው ነጥብ ቢኖር በሙስሊሙ ላይ በየትምሕርት ተቋማት የሚፈፀመው ጥቃት እኮ በመንግስት በራሱ ገና ትግሉ ሳይጀመር አንስቶ ረቂቅ ተበጅቶለት በፕላን የሚደረግ ስልታዊ ጭቆና ነው። እርግጥ ነው ትግሉ ከተጀመረ በኋላ የሰማናቸው የተለያዩ ጭቆናዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግና ትግሉ ከመጀመሩ በፊትም እኮ ብዙ በደል እና ጭቆናን ስንሰማ ቆይተናል ለነዛ ሁሉ ጭቆናዎች መንግስት ተገቢውን ማስተክካከያ ሊያደርግ ይቅርና ጭቆናዎቹ የሚበረቱበት የህግ ድጋፍ ለመስጠት ረቂቅ በማዘጋጀት ላይ ተጠምዶ እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ነው።ትግሉን ማቆማችን ለታቀደልን ተንኮል የተሻለ ሜዳ ይፈጥር እንደሆን እንጂ አያበርደውም።

ዘጠኝ “…የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት ወደ ፅንፈኛ አለማዊነት መምራት…” በዚህ ክፍል ውስጥ ደግሞ መንግስት ፀረ ሀይማኖት አቋም እንዲይዝ ትግሉ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይለናል። ይገርማል የምንታገለው የተሻለ ነፃነትን ለማግኘት እንጂ ይበልጡኑ ለመጨቆን እኮ አይደለም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ሙስሊሙ ጭቆና በዛብኝ ብሎ የታገለባቸው አጋጣሚዎች ከሞላ ጎደል አንፃራዊ መሻሻልን አስመዝግበውለታል የ66ቱን ትግል እንኳ ብንመለከት ሰላማዊ ሰልፍ ከተደረገ በኋላ ጨቋኙ የዐፄ ስርዓት መጠነኛ ለውጦችን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ለማስገኘት ተንቀሳቅሷል። እርሱ ተገርስሶ የደርግ ስርዓት ሲመጣ ደግሞ የስርዓቱ አምባገነንነት እንዳለ ሆኖ ለሙስሊሞች ብዙ መብቶችን ለማረጋገጥ ተገዷል። ዛሬም የኛ ትግል ከአባቶቻችን በወረስነው ፅናትና አልበገር ባይነት ተጉዘን የተሻለ ነፃነትን ማግኘት እንጂ ትግላችን የመንግስትን ባህሪ ይበልጥ ያከፋዋል የሚል እምነት የለንም። ያም የሚሆን ከሆነ ይበልጥ ትግላችንን የምናጠናክር ይሆናል። እንዴ:- መንግስት እኮ በኛው በጎ ፍቃድ የሚመራን አካል ነው ካልተመቸን ታግለን ልንቀይረውም እንችላለን። እርግጥ ነው እንዲህ ያለው ሀሳብ ለፀሀፊው የህልም ዓይነት ነው፤ በጣም የሚያሳዝነው ነገርም ሰዎች በአላህ ላይ ተስፋ ቆርጠው ከዛ በተቃራኒ የፍጡራን ስብስብ በሆኑ ፓርቲዎች እና መንግስታት አይነኬነት ላይ ወሰን ያለፈ መተማመን ሲኖራቸው ማየት ልብ ይነካል። ታሪክን ያነበበ ሰው እኮ ከኢህአዴግ በብዙ እጥፍ ይሻሉ የነበሩ ኢምፓየሮችን በቀላሉ ሲፈራርሱ መመልከት የተለመደ ነው ግና ወደኛ ሲመጣ ጉዳዩን ልክ ከሀዲያን ህዝቦች እንዳሉት “..ሀይሀት ሀይሀተ ሊማ ቱዓዱን…” አድርገን ማሰባችን በአላህ ላይ ተስፋ መቁረጥን ያሳብቅብናል።

አስር “…ፅንፈኛ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆን…” በዚህ ክፍል ስር ለተጠቀሱት ምክንያቶች ሰበቡ በሰለጠነ አካሄድ መብቱን የሚጠይቀው ህዝብ ሳይሆን ለህዝብ ድምፅ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው መንግስት ነው በመሆኑም እራሱ ያመጣውን ጣጣ መሸከም የራሱ ሀላፊነት ነው።

አስራሀንድ “…የመከፋፈል አደጋ…” እዚህ ክፍል ላይ የቀረበው ጥርጣሬ (ዞን) ነው አሁን ያለው ተጨባጭ (የቂኑ) ደግሞ አንድነታችን ነው ይኸው ፅሁፍ ባስቀመጠልን የፊቅሁል አውለውያት መመዘኛ መሰረት ለተጨባጩ ቅድሚያ በመስጠት ትግላችን አንድነታችንን የሚያጠነክር እንጂ ክፍፍል የሚያመጣ እንዳልሆነ ማስቀመጥ ይቻላል።

አስራ ሁለት “…የአወሊያ ንቅናቄ የብሔራዊ ደህንነት ጠንቅ ተደርጎ ቀርቧል።…” እዚህ ቦታ ላይ ቀላል ጥያቄ እናንሳ ይህንን ያለው ማነው??? ምላሹ መንግስት የሚል ነው የሚሆነው። እኛ ደግሞ እየታገልን ያለነው ይህንን ያለውንና መብታችንን የጨፈለቀውን መንግስት ነው። ስለዚህ የራሱ እንቶፈንቶ ወሬ ራሱን ከመታገል ሊያቅበን አይችልም እርሱማ እኮ የሀገር ብቻ ሳይሆን የአህጉርም ስጋት አድርጎ ሊስለን በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ላይ ታች ሲሯሯጥ ነበር። ባይሆን በኛና በፅሁፉ አቅራቢ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የፅሁፉ አቅራቢ የፍጡራን ስብስብ የሆነውን መንግስት አግዝፎ በማየት በርሱ ላይ ተስፋ መቁረጡና እኛ ደግሞ በተቃራኒው በአላህ ላይ ተስፋችንን አድርገን እርሱ በሻው መንገድ ነፃነታችንን እንዲያጎናፅፈን መሻታችን ነው።

IV. የቀረቡት የመፍትሔ ሀሳቦች

ፅሁፉ ለትግላችን መቆም ያቀረባቸው አንኳር መከራካሪያዎች ከላይ መልስ የተሰጣባቸው ሲሆኑ በቀጣይ መፍትሔ ተብለው በቀረቡት ሀሳቦች ላይ ያለኝን ጠቅላይ ምልከታ ላስፍር።
በመፍትሔነት የቀረቡት ሀሳቦች በሁለት ጎራ የሚከፈሉ ሲሆን አንደኛው የተቃውሞው መቆም ላይ ተንተርሶ መፍትሔ የሚለውን ሲዘረዝር ሁለተኛው ክፍል ፈዳኢለል አእማልን እንደመፍትሔ ያቀርባል።

በተቃውሞው መቆም ላይ የተንተራሱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ከላይ በዝርዝር ላሳየሁት ምላሽ ሲባል አልቀበላቸውም። ከዛ ውጭ ስገዱ፣ ፁሙ፣ ሲዋክ ተጠቀሙ፣ ጁምዓ ጁምዓ ገላቹን ታጥባቹ ንፁህ ልብስ ልበሱ፣ ቅሩ እና መሰል ይዘት ያላቸውን ፈዳኢለል አእማላት እንደትግላችን አንድ ግብዓት ልንጠቀምባቸው እንቻላለን። ምናልባትም አሁን እየደረሰብን ያለው ችግር በወንጀላችን የተነሳ ሊሆን ስለሚችል በመልካም ስራዎች ወደ አላህ የመቃረቢያ አቅጣጫዎች ያስፈልጉናል ይህንንም በድምፃችን ይሰማ ገፅ አስታዋሽነት ስንፈፅም ቆይተናል ወደፊትም እንገፋበታለን። ግና በእነዚህ ስራዎች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ትግል ማድረጉ ይቁም ማለት አግባብነት የለውም። ፈዳኢለል አእማላት ብቻቸውን ከጭቆና የሚታደጉ ቢሆን ኖሮማ በአላህ መንገድ ላይ መታገል የሚባል ዒባዳ በዲናችን ውስጥ ባልተደነገገ ነበር መቼም ምንም ያህል መልካም ስራዎችን ብናበዛ ከነብዩ (ሰዐወ) እና ከባልደረቦቻቸው ልንልቅ አንችልም ግና መልእክተኛው (ሰዐወ) እና ባልደረቦቻቸው ከነዛ ሁሉ መልካም ስራዎቻቸው ጋር ጭቆና ይደርስባቸው ነበር ይህንንም ከለያቸው ላይ ለማስወገድ ወደ አላህ ከመቃረብ ጎን ለጎን በአላህ መንገድ ላይ ይታገሉ ነበር። ስለዚህ እኛም ወደ አላህ መቃረቡን እንደ ትግላቸን አንድ ግብዓት እየተጠቀምን ጎን ለጎን በአላህ መንገድ ላይ ትግል ማድረጋችንን ግን አናቆምም።

V. ማጠቃለያ

ጦርነቱ ከተስፋችን ጋር ነው!!!
እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብታችን ይከበር ብለን ድምፅ ማሰማት ከጀመርን እንሆ አመት አልፎናል ። ታድያ ይህንን ግዙፍ የሰው ሀይል (አርባ ሚሊየን የሚገመት) በማሰርም ይሁን በመግደል ማሸነፍ እንደማይቻል ጠላቶቻችን አስቀድመው አውቀውታል ምክንያቱም ይህን ያህል ሰው ለመግደል በቂ ጥይት ለማሰር ደግሞ በቂ እስርቤት የለም በመሆኑም በማንኛውም አይነት መለኪያ ከዚህ ግዙፍ ህዝብ ጋር መጋፈጥ ውጤቱ ሽንፈት መሆኑን ጠላቶቻችን አስቀድመው ተረድተውታል። በመሆኑም ጠላቶቻችን ከህዝቡ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ ህዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ ለድል እንደሚያበቃቸው አስበዋል። በመሆኑም እያንዳንዱዋ እየተጓዙት ያለው እርምጃ ህዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ የታለመ መሆኑን ተረድተን ምንም አይነት ፈተና እና ችግር ቢገጥመን ተስፋ ከመቁረጥ እራሳችንን ልናቅብ ይገባናል። ከዚህ በታች የተወሰኑ ህዝቡን ተስፋ የማስቆረጫ ስልቶቻቸውን እጠቅሳለሁ፤ ሁሉም ማህበረሰብ ይህንን ተገንዝቦ ለነዚህ ስልቶች ባለመሸውድ ህይወቱ እስካለች እና ያነሳው የመብት ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ እራሱን በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ ለማቆየት ቆርጦ ሊነሳ ይገባል። ጠላቶቻችን የኛን ቆርጦ መነሳት ካዩ እነርሱ ተስፋ መቁረጣቸው አይቀርም። በመሆኑም በአላህ(ሱወ) ፍቃድ ድል የኛ ይሆናል።

ተስፋ ማጨለሚያ ስልቶች

1ኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎችን አስቀድሞ ተስፋ ማስቆረጥ
የዚህ መላ ዋነኛ ማጠንጠኛ በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ህዝቡን መምራት የሚችሉት ከማህበረሰቡ ውስጥ ሁለት ፐርሰንቶቹ (2%) ብቻ ናቸው የሚለው እሳቤ ሲሆን እነዚህን ሁለት ፐርሰንት ሀይላት ተስፋ ማስቆረጥ ከተቻለ ህዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ እንደሚቻል ይታመናል። በዚህ እሳቤ መነሾነትም መንግስት የተለያዩ ተፅእኖ ፈጣሪ የተባሉ ግለሰቦችን ተስፋ ለማስቆረጥ ተሯሩጧል፤ ኮሚቴዎቻችን ከመታሰራቸው በፊት በደህንነት ሀይላት ይደርስባቸው የነበረው ማስፈራሪያና እንግልት፣ ከታሰሩም በኋላ የደረሱባቸው ስቃዮች ዋነኛ አላማ እነርሱን ተስፋ በማስቆረጥ የነርሱን የጨለመ ተስፋ ወደ ማሕበረሰቡ ማውረድ ነበር፤ ግና አልሀምዱሊላህ በኮሚቴዎቻችን ፅናት ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ አልሳካልህ ያለው መንግስት ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም ከኮሚቴው ውጭ ያሉ የተለያዩ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ የተባሉ ግለሰቦችን ተስፋ ለማስቆረጥ ብዙ ርቀት የሔደ ሲሆን ተሳክቶለትም የተወሰኑ ግለሰቦችን ተስፋ ማስቆረጥና የእርሱን (የመንግስትን) ግዝፈት በማሳመን በአላህ ሁሉን ቻይነት ላይ ተስፋ ማስቆረጥ ችሏል። ዶ/ር ኢድሪስ በሬድዮ ቀርቦ መንግስትን ከሚያክል አካል ጋር ትግል መግጠም አያዋጣም ሲል የተናገረው ንግግርም ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል። ዛሬ ላይ ደግሞ ታላቁ ሸሀችን ሀሰን ታጁም ሳያውቀው የዚህ ስትራቴጂ ሰለባ እንደሆነ ግምት መውሰድ ይቻላል፤ እናም እኔ በግሌ ለሸሁ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት ቢኖር ዛሬ የደረስክበት አቋም ላይ እንድትደርስ ያደረጉህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ባምንም በዙሪያህ ያሉ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ጫና ግን ዋነኛውን ቦታ ሊይዝ እንደሚችል እገምታለሁ እናም ኡስታዙና አብሽር ነስር እየቀረበች ነው አንተም ለኢስላም ተጨንቀህ ይጠቅማል ያልከውን ሀሳብ በመሰንዘርህ አላህ በመልካሙ እንዲመነዳህ እየለመንኩኝ ግና የፅሁፍህ አጠቃላይ መንፈስ ተስፋ ቆርጦ ተስፋ ለማስቆረጥ የሚታገል በመሆኑ ከዚህ የተስፋ መጨለም አለም ወጥተህ በአላህ ሁሉን ቻይነት ላይ ተስፋህን እንድታደርግና ሰዎችን ወደኸይር በተጣራህበት አንደበትህ ነስሩን እንድትለምንልን ጥቆማዬን ማቅረብ እሻለሁ።

2ኛ ትንሽነት እንዲሰማን ማድረግ
ይህ ስልት መንግስት ተግላችንን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ሲጠቀምበት ያለ ስልት ነው። አንድ ግለሰብ በማህበረሰብ ውስጥ የሆነን ለውጥ ማምጣት ፈልጎ መላው ማህበረሰቡ ከርሱ በተፃራሪ ቢቆምበት ተስፋ የመቁረጥ እድሉ በጣም የሰፋ ነው። በዚህ አግባብም መንግስት የመብት ጥያቄን አንግቦ የተነሳውን ማህበረሰብ ትንሽነት (ጥቂትነት) እንዲሰማውና ተስፋ እንዲቆርጥ ብዙ ሴራዎችን የሰራ ሲሆን ዝወትር ከአንደበቱ ከማትጠፋው ጥቂቶች ከሚለው ቃሉ አንስቶ በተለያዩ ክፍለ ሐገራት ያሰናዳቸው ድራማዊ ተቃውሞ ሰልፎች፣ በየሚዲያው ከህዝብ የተሰጠ አስተያየት እያለ የሚያቀርባቸው ሀሳቦች እና መሰል እርምጃዎቹ መብቱን የጠየቀው የሕብረተሰብ ክፍል ትንሽነት እንዲሰማውና ተስፋ እንዲቆርጥ ታልመው የሚሰሩ ሴራዎች ናቸው።

3ኛ አቅመ ቢስነት እንዲሰማን ማድረግ
ህዝበ ሙስሊሙ በሐገሪቱ ውስጥ ካለው የህዝብ ብዛት አንፃር አንዲትም እንኳ ጠጠር ሳይወረውር ጠላቶቹን የመርታት አቅም ቢኖረውም ነገር ግን ጠላት ሆን ብሎ ሙስሊሙ በአንስተኛ መጠን በተሰባሰበባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በማሰር እና በመግደል ምንም አላመጣም የሚል ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ከሚጠቀሙባቸው ተስፋን የማስቆረጫ ስልቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው በአሩሲ አሳሳ፣ በዓንዋር፣ በአወሊያ፣ በደሴ እንዲሁም በወሎ ደጋን እና ገርባ የተደረገው ጭፍጨፋና ግድያ የዚሁ ስልት አካል ነው።

4ኛ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ የህዝቡን ስነልቦና መውሰድ
ይህ ስልት ያሰቡትን ያህል ማሳካት ያልቻሉት ስልት ሲሆን በዚህ ስልት ስር የሚካተቱ ተግባራት የጦር መሳርያ ሰብስቦ ቀርጾ በሙስሊሙ ላይ ማላከክ፣ ሽንኩርት ለመከተፍ የገባን ቢላዋ እንደጦር መሳርያ ትጥቅ ማሳየት፣ ቡግሩ ፈንድቶ አንገቱ ላይ ፕላስተር የታሸገን ፌደራል በህዝብ እንደተደበደበ አድርጎ ማቅረብ፣ የህዝብ መገልገያ ንብረቶችን የማውደም ድራማ መስራት እና መሰል ድርጊቶች የሚካተቱ ሲሆን አላማቸውም በትግሉ ውስጥ ያሉትን እንዲሁም የትግሉን ደጋፊዎች ትግሉ መስመር እየለቀቀ እና ከቁጥጥር እየወጣ እንደሆነ እንዲያስቡ በማድረግ እራሳቸውን ከትግሉ ተስፋ በመቁረጥ እንዲያገሉ ማድረግ ነው።
“ወላ ተሂኑ ወላ ተህዘኑ ወአንቱሙል ዓእለውነ ኢን ኩንቱም ሙእሚኒን”
“ተስፋ እንዳትቆርጡ እንዳትተክዙም አማኞች ከሆናቹ የበላዮች ናችሁ”

ተፈፀመ!!!

————————-

የተደፋው የሃሰን ታጁ ቀለም ሲታፈስ/ክሽፈት 1/

የአላህ ራህመትና እዝነት ለተወዳጁ ኡስታዜ ይሆን ዘንዳ ዱዓዬ ነው! ሀሰን በአላህ ይሁንብኝ ለአላህ ብዬ በጣምም እወድሃለሁ! ለአንተ ያለኝን ክብርና ሞገስ ብዕሬ ልትከትብ ይሳናታል ግና መምህር ሆይ! ለአንተ ያለኝ ፍቅርና ሞገስ የከሸፈች ብዕርህን ከመተቸት እንዳያሳብዬኝ አንተው ባስተማርከኝ መሰረት እንዲህ ስል ብዕርህ መክሸፏን አሊያም ጉዞ ወደ መክሸፍ ማለቷን አሳውቅሃለሁ፡፡ልሒቅነትህ የኔን የአፃፃፍ ድክመት እንደሚረዳኝ በማሰብም ፅሁፍህን በገባኝ መልኩ አብጠልጥየዋለሁ፡፡

ኡስታዝ ሀሰን ታጁ የፃፈውና በነ አቢይ ጣሰው ለህዝብ ይፋ የሆነውን ፅሁፍ ባነበብኩ ጊዜና ተገረምኩም እራሴንም ጠየቅኩም ግና ፅሁፉ የሀሰን ታጁ ብዕር መክሸፏን አበሰረኝ፡፡ሀሰን ይህ የተቃውሞ አካሔድ ሌላ መንገድ ቢፈለግለት ይልና በተለይም የጁሙዓ ተቃውሞዎች መቋረጥ እንዳለባቸው አልፎም ኮሚቴዎቹን ለይቅርታ ያቅዳቸዋል።ለትነተና እንዲመቸውም ሁለት ቡድኖችን ፈጥሯል አንደኛው ተቃውሞው እንዲቀጥል የሚፈልግ ወጣትና ሁለተኛው ደግሞ ተቃውሞ ይቋረጥ የሚሉ ልሂቃን ናቸው።

እንግዲህ ከዚህ ይጀምራል የሀሰን ብዕር ክሽፈት ወጣቶችን አላዋቂ፣ስሜተኛ፣ጃሂል አድርጋ ለማቅረብ ሞክራለች አሊሞች ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ብሎ የሰየማቸው ቡድኖች ደግሞ የሀሰን ሃሳብ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆኑ በወጣቱ ላይም ጣት የሚቀስሩ ናቸው።በዚህ ፅሁፉ ጃሂልና ዓሊም ብሎ ቢከፍለው የተሻለ ይሆን ነበር! ያ ካልሆነ ግን ሀሰንን ያገኙት ወይም ያገኛቸው ወጣቶች (ተቃውሞ እንዲቀጥል የሚሹት) ፅኁፉ በገለፃቸው የአስተሳሰብና የእውቀት ደረጃ ካሉ ኡስታዝ ውሎው ከማይማን ጋር ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡የተሳሩ ወንድሞቻችንን ግፍ እንበቀላለን፣መንግስትን እንጥላለን፣ሙቀቱ ደስ ይላል፣መንግስትን እናናደውና ተቃውሞውን እንደበቅበታለን በሚል የአስተሳሰብ ምንዱባን ውስጥ ሆነው ይህን ታሪካዊ ትግል የተቀላቀሉ ወጣቶች እንኳን በኡስታዝ ዙሪያ በኔ በኩል ካሉ “ኢትዮጵያችን የት ነው ያለችው?” ያስብላል።እኔ የማውቃቸው ወጣት የትግሉ አጋሮች የሚታገሉበት የጠራና ውሃ የሚቆጥር ዓላማ አላቸው።ይህም ኢህአዴግ በኢስላምና በሙስሊሞች ላይ የሚያደርገውን ጭቆናና ግፍ መቃወም ነው።እናም ለኡስታዝ የምለው አንተ የጠቀስካቸው ወጣቶች እንደ ህዝብ ባይጠፉም እንደ አቢይ የትግሉ አራማጆችና ተዋናዮች ግን የሉም ነው!

የብዕሯ ክሽፈት ግን ጡዘቱን የነካው አሁን ላይ የበኩር ጥያቄዎቹ ሞተዋል በማለቷ ነው። እኔ ግን እላለሁ ጥያቄዎቹማ ከጥንት ልፍስፍስ ጮርቃነታቸው ጎልምሰውና ደርጅተው ዛሬ ጥርስ አውጥተዋል! ከተራ የመጅሊስና የአወሊያ ጥያቄ ወደ ኢስላምና ሙስሊሞች ህልውና ይከበር ተቀይሯል።

የአህባሽ በሃይል ለመጫን የተደረገው ሙከራ የሀሰን ብዕር እንደከተበችው ሞቶ አልተቀበረም ይልቁንም ይበልጥ ጉልበቷን ጨምራ አቅሟን አደርጅታ በአራት ኪሎ አፈሙዝ ጦንችታለች ተገዳዳሪዎቿን አንድም ወደ ስደት አንድም ወደ ግዞት አግዛ ያለ ተቀናቃኝ በየመሳጅዳችን ገብታለች።የነ አህመድን ጨሎ ድንበሯን አልፋ ከገጠር እስከ ከተማ ባሉ ማሳጅዶቻችንና አቢዮታዊ አህለ ሱና ወልጀመዓ አደረጃጀት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ደርጅታለች? እና ኡስታዜ እኛ ወይስ የአህባሽ ጉዞ ሞቶ የተቀበረው? አህባሺያኑ ዙፋን ተሰጥቷቸው በኮሚቴዎቻችንና በቀለም ቀንድ ዓሊሞቻችን ላይ የ”ሚህና” ችሎት ጥለው ችሎት ላይ በተሰየሙበት ወቅት እንዴትስ የሀሰን ብዕር የአህባሽ ጉዳይ ሞቶ ተቀብሯል ልትለን ቻለች? ምኑ ነው የሞተው ብዬ እንዲጠይቅ እገደዳለሁ ሱሪውን ያሳጣረ፣ፂሙን ያንዠረገገ፣አህባሽኛ ወግ ያልጠረቀ፣እጁን በኮሚቴው ላይ ያልቀሰረ፣ለሚህናዊው ችሎት እውቅና ያልሰጠ ሁሉ ጠዋት ወጥቶ ማታ ቤቱ በሰላም ስለመመለሱ እርግጠኛ ባልሆነበት ወቅት አህባሽ እንዴት ሞታል ልትለን ቻለች ብእሯ?

እቃ እቃ ነው ምርጫ?
የኡስታዝ ብዕር ተቃቀውሞው መጅሊስን የምርጫ ባህል ማስቀየር መቻሉን ይጠቅስና ከአንግዲህ “የእድሜ ልክ መጅሊስ” አይኖረንም ይላል፡፡…ይቀጥልናም “በሂደቱ ያለን ቅሬታ እና አስተያየት እንዳለ ሆኖ ወደ ኋላ መመለስ ይቻላል ብዮ ግን አላምንም” ይላል! እኔ ግን እላለሁ የመጅሊስን የምርጫ ባህል ከመስጅድ ወደ ቀበሌ መዞሩ አሊያም ፍፁም የልጅ እቃ እቃ የሚመስል ምርጫን እንደ ልዩ ለውጥ አድርጌ መቀበል አልችልም።ሰፊውን ሕዝበ-ሙስሊም ያላሳተፈ፣በኢህአዴጋዊው አህለ-ሡና ወልጀመዓ የተደራጁ ሙሾ አውራጆችና የመለስ ሙት መንፈስ አምላኪዎች (ኦኩንቶች) ከቀበሌ የተሰገሰጉበትን ምርጫ እንዴትስ ልዩ ለውጥ ያመጣ ልንለው እንችላለን? ለኔ ግን የአሁኑ ምርጫ የሚሰጠኝ ትርጉም ሌላ ነው! መንግስት ሙስሊም ዜጎቹን የናቀበትና በግልፅ ያዋረደበት! ኦርቶዶክሱን በቀበሌ ወይም ሌላውን በቀበሌ ብሎ የማይሞክረውን በሙስሊሙ ላይ እውን አድርጎታል ይህ ፍፁም ንቀት ነው! በደልም ነው!ከአሁን በኋላ የእድሜ ልክ መጅሊስ ባይኖረን የእድሜ ልክ ቁጭትና የቀበሌ ምርጫዎች ግን ይኖሩናል! የኡስታዝ ብዕር በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ያሳረገችው ታሪክ አይለወጥም ወግ በእርግጥ ያስደነግጣል? እኔ ግን እላለሁ ለምን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም? ወቅትን መመለስ ባንችልም የምርጫውን ንቀትና ጉድፎች ግን መልሰን አራት ኪሎ እንዲሰበሰቡ ማድረግ እንችላለን።የሙስሊሙን ድምፅ ግን ከቀበሌ ወደ መሳጅዶቻችን መመለስ እንችላለን። የኢህአዴግን ስውር እጆች ወደ ብብቶቻቸው እንዲመሰሉ ማድረግ ግን እንችላለን።
የኡስታዝ ብእር ክሽፈቷን ቀጥላለች አዲሱ መጅሊስ ለውጥ ላይ ነው ትለናለች! “በአዳማ ያደረጉት ጉባኤ አጠቃላይ መንፈስ መጅሊስ የአቅጣጫ ለውጥ እያደረገ መሆኑን አመላካች ነው።” የኡስታዝ ሀሰን ብእር ለውጥን እንዴት ነው ያሰላችው? ዛሬም ድረስ አህባሽ የመጅሊሱ ኦፊሲያሊያዊ እምነት ሆኖ ሌላው ጀመዓ ወደ ስደትና ግዞት እንዲገፋ የሰቆቃው ባለድርሻ በሆኑበት ወቅት እንዴት ለውጥ ላይ ናቸው ለማለት የሀሰን ብዕር ደፈረች? ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለማእከላዊው ጓንታናሞ ሲገበሩ ሙስሊም ልሒቃን በመንግስት ሚዲያ ሲብጠለጠሉና ሲበየኑ ከዳር ሆኖ የሚዲያ ጉልበት የሆነ ድርጅት፣ሙስሊም ምሁራንና ሰራተኞች በየስራ ቦታቸው በስም በፂማቸው፣በሒጃብ ኒቃባቸው የእነ እነቶኔ ጣት ሲቀሰርባቸውና ሲባረሩ አንዳችም ለማለት ያልደፈረ ሺባ አደረጃጀት እንዴት እራሱን ማቅናት ይቻለዋል? መንግስት በሙስሊም ህዝቦቹ ላይ ዳግማዊ ቀይ ሽብርን ሲያውጅ፣በህዝቦች መካከል የኢንተርሀምዌ ሽል ሲጠነስስ ሃግ ያላለ! የኡማውን ጩኸትና እንባ ከመጤፍ የቆጠረ መጅሊስ እንዴት ለውጥ ላይ ነው ብሎ አሰበ? አዲሱ አመራር ከመጣ ወዲህ የድሮዎቹ አመራሮች ያሳሰሯቸውን ኮሚቴዎች ለማስለቀቅ ምንስ ጥረት አደረገ? እንጃ! ብቻ የሀሰን ብዕር ክሽፈቷ አስደንጋጭ ነው።

የሀሰን ታጁ ብዕር ኢህአዴግን ፈፅማ አታውቀውም “የሃገራችን የሴኪዩላር ስርኣት ኢ-ሃይማኖታዊ ሲሆን ግብግቡና ጭፍጨፋው ከተራዘመ ግን ወደ ሁለተኛው ዓይነት(ፀረ-ሐይማኖታዊ) ሴኪዩላሪዝምነት ልንገፋው እንችላለን።” ብላ ፅፋለች። አዎ! የኔና የኡስታዝ ትልቁ ልዩነት የሚመነጨው ከዚህች መሰረታዊ አስተሳሰብ ነው። እኔ ባሉኝ መረጃዎች የኢህአዴግ መንግስት በተለይም በኢስላም ላይ የሚከተው ርዕይት ፀረ-ሐይማኖታዊ እንጅ ኢ-ሐይማኖታዊ ፈፅሞ አይደለም።ኢ-ሐይማኖታዊ ሴኩዩላሪዝም “አትንካኝ አልነካህም! እጅህን አውጣ እጄን ላውጣ!” ከሚል ጭብጥ የፈለቀ ነው! ታዲያ ኡስታዝ ኢህአዴግ ኢስላምን ለማንኮታኮት አልተንቀሳቀሰም እያልከን ነው? ሒጃብና ሶላትን በህግ ለመከልከል አልሞከረም አያልከን ነው? ከቁርዓን የተመዘዙ ከሀዲስ የተሳቡ ጥቅሶች የአሸባሪነት ምንጭ ሆነው የፀረ-ሽብር ህግ አንቀፅ ተጠቅሶባቸው ሙስሊሞችን ወደ ዘብጢያ እንዲወረወሩ አልተደረገም እያልከን ነው? በጁሙዓ ኹጥባ አቢዮታዊ ዴሞክራሲ አልተሰበከም አያልከን ነው? ዱዓቶች በመስጅድ ውሥጥ ዳዕዋ እንዳያደርጉ ኢህአዴግ መራሹ መጅሊስ ህግ አላወጣም እያልከን ነው? ዲናችን በኢህአዴጋዊ አመዳደብ ነባርና አዲስ? ኢትዮጵያዊና የውጭ?…ተብሎ ደረጃ አልወጣለትም እያልከን ነው? በእረግጥ ይህን አንተም ፅሁፍ ላይ አይቻለሁ በአላህ ፈቃድ ክፍል ሁለት ትችቴ ላይ አቀርበዋለሁ፡፡