ከሰው ላይ ይልቅ ሀሳብ ላይ እናተኩር!

ከሰሞኑ በወንድም ሀሰን ታጁ ቀረበ የተባለ ጽሁፍ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሁፍ በውስጡ የተለያዩ ሀሳቦችን ይዟል፡፡ እኛ የሀሰን ታጁን ሀሳብ አስመልክቶ ዝርዝር ሀሳቦችን ከመሰንዘራችን በፊት አንድ አንድ ጠቃሚ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኛም ሆንን ብዙዎች ከጽሁፉ ይዘት በመነሳት ይህ ጽሁፍ በእርግጥ የወንድም ሀሰን ታጁ ነው? ብለን ለመጠየቅ እየተገደድን ነው፡፡ ምክንያቱም የምናውቀውና የምናከብረውን ሀሰን ታጁ በዚህ ጽሁፍ ልናገኘው አልቻልንምና፡፡ ሆኖም ወንድም ሀሰን ጽሁፉን ራሱ በአካልም ጭምር ለተለያዩ ወንድሞች እያሰራጨው እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ከዚህም አልፎ ወንድም ሀሰን ከትላንት ረፋድ ጀምሮ በራሱ የፌስ ቡክ አካውንት በመምጣት ጽሁፍን ለማስነበብና ለማወያየት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ በመግባባት ላይ የተመሰረተን ሰላማዊ ውይይት የሚጠላ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ጽሁፉ ይህን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመንቀፍና በመዝለፍ አጉል ስምም በማሰጠት እንዲሁም በሙስሊሙ ህብረተሰብ በጥሩ ጎን በማይታዩ ግለሰቦች አማካኝነት ነበር ወደ ፌስቡክ የመጣው፡፡ ሆኖም ይሄ ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ታርሞ ወንድም ሀሰን በራሱ ሀሳቡን ለማንሸራሸር ወደ መድረኩ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ በዚህ ጊዜ ይዞ መምጣቱ ሊፈጥር የሚችለውን ፊትና መዘዙም እሱን ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚችል ምን ያህል አስቦበታል ለሚለው በቂ ምላሽ የለንም፡፡ ምንአልባትም በዚህ ጉዳይ ወንድም ሀሰን ምላሽ ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 

አንድ አሳሳቢ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም ወንድም ሐሰን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴውን በአውንታዊ መልኩ ሲመለከትና ምሁራዊ ድጋፉንም ያበረከተለት ትግል ዛሬ በጽሁፍ ደረጃ ማጥላላት መጀመሩ ሊፈጥርብን የሚችለው የራሱ ንዴትና እልህ ይኖራል፡፡ እንደውም ብዙ ወንድሞች ይህ ጽሁፍ የወንድም ሀሰን አይደለም፣ መንግስትና በዙሪያው ያሉ ሰዎች በግዳጅ በእሱ ስም እንዲወጣ ያደረጉት እንደሆነ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህን በሂደት የምናየው ነው፡፡ ጽሁፉ የሀሰን አይደለም የሚባለው የያዘው ሀሳብ እንኳን ከሀሰን ታጁ ይቅርና ግንዛቤው ዝቅ ያለም ሰው ሊያነሳቸው የማይደፍራቸው ሀሳቦች ያዘለም በመሆኑ ነው፡፡ ወንድም ሀሰን ቃሊቲ ከሚገኙ ኮሚቴዎቻችንም ጋር ተነጋግሮ መስማማት እንዳልቻሉ ከታማኝ ምንጮች ተሰምቷል፤ በጽሁፉ ስሜታቸው በጣም እንደተጎዳም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሆኖም በዚህ ጽሁፍም ሆነ ሁኔታ በመናደድ ሀሰን ታጁን በክፉ ቃላት መጥራት፣ በሌላ መልኩ መዝለፍ፣ ማራከስና ማንጓጠጥ በፍጹም ተገቢ አይሆንም፡፡ ይህን የምንለው ጥቂት ወንድሞች መሰል ተግባሮችን ሲፈጽሙ በማየታችን ነው፡፡ ሀሰን ታጁ አሁን ምንም ይበል ምን ለኢትዮጽያውያን ሙስሊሞች ትልቅ ውለታ የሰራ ወንድም መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ሀሰን እኛ ሙስሊሞች በአማርኛ ስነ ጽሁፍ አሻራ እንዲኖረን የተጋ እና ሲተጋም የኖረ ወንድም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ70 በላይ መጻህፍትን ተርጉመዋል ተብለው አሁን በህይወት የሌሉት አቶ ማሞ ውድነህ ተደጋግሞ ስማቸው ይነሳል፡፡ ወንድም ሀሰን ታጁ ግን ከ110 በላይ መጻህፍትን በማዘጋጀትና በመተርጎም ልፋቱን በተግባር ያስመሰከረ ወንድም ነው፡፡ የእሱ ስራዎች ያልገባበት ቤት የለም፣ መጻህፍቱ ያልዳሰሷቸው ዲናዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አጀንዳዎች የሉም፡፡ ስለዚህ ያነሳውን ሀሳብ ከመተቸት በዘለለ ወደ ሰብእና ጉዳዮች በመግባት እሱን ለማሳጣት መሞከር ብዙ ክፍያ ያስከፍለናል፣ ሀሰንን ማጣት የመንግስትን ፍላጎትም በተዘዋዋረ ማሳካት በመሆኑ በጣም በጣም ጥንቃቄ እናድርግ፣ በአላህም ዘንድ ያስጠይቀናልና፡፡

 

በመሰረቱ ሐሰን ያነሳቸው ሀሳቦች አዲስ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያልተፈተሹ አይደሉም፡፡ እውነቱን ለመናገር ይሄን ጽሁፍ የሀሰን ነው ብለን ስንናገር የሀሰንን ክብር ያወረድን እየመሰለን እንሸማቀቃለን፡፡ ፍትህ ሬዲዮ በዛሬ ፕርግራሟ ለሀሰን ታጁ ጽሁፍ ምላሽ አትሰጥም፡፡ በአላህ ፈቃድ በቀጣዮቹ ቀናት እኛም ሆንን ሌሎች ወንድሞች የማያዳግም ምላሽ እንደሚሰጡበት አንጠራጠርም፡፡ ይህን የምንለው የሀሰን ታጁ ጽሁፍ ጠጣር ሀሳብ ባለማንሳቱም ጭምር ነው፡፡ ሐሰን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ሲሰራ ተመልክተናል፡፡ በቅርቡ ለንባብ ያበቃውን እንኳ ‹‹ሺአ›› የተሰኘውን ልዩ የምርምር ስራ ተመልክተናል፡፡ ሀሰን ሲሰራ በዛ መልኩ እንደሆነ ነው የምናውቀው፡፡ ይህ ጽሁፉ ግን እንኳ የሀሰን ይቅርና የምሁር እጅም አይንም ያላረፈበት የሚመስሉ ግዙፍ የመረጃ መጣረሶች፣ የእይታ መዛባቶች፣ የምርምር ስራዎች መሰረታዊ ህግጋትን ያላካተተ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሀሰን ጽሁፉንም ሆነ ሀሳቡን ማስፈር የጀመረው እንቅስቃሴውን ማስቆም ይኖርብናል በሚል መነሻ በመሆኑ ሲበዛ ማስቆሚያ መንገዶችን ለማስቀመጥና አንባቢን ለማሳመን ሲለፋ እንመለከተዋለን፡፡ ግን የሚሳካለት አልሆነም፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር የተፈጠረው ከሀሰን ሳይሆን ካነሳው ሀሳብ ጠባብነት የተነሳ ነው፡፡ ሀሰን በጽሁፉ የእሱን ሀሳብ ለማስረጽ ብዙ ብዙ ቢለፋም ኢላማውን ሊመታ አልቻለም፤ ምክንያቱም ሀሳቡ አንካሳ ነው፡፡ የሀሰን እናቁም የሚለው ዋነኛው መደምደሚያ ሀሳቡ ሁለት እርምጃ እንኳ የሚያስኬድ አይደልም፡፡ ለምሳሌነት ሀሰን ዋነኛ መከራከሪያ ያደረገውን የአሕባሽ ስልጠና መቆም ጉዳይ ብትመለከቱ ሀሰን ገና ሀሳቡን ማሰራጨት በጀመረ ሳምንት ነው መንግስት የአሕባሽን ስልጠና በጦላይ ማሰልጠኛ ተቋም በሚሥጥር እየሰጠ እንደሆነ የተረጋገጠው፡፡

ከዚህ በላይ ግን ሀሰንም ሆነ ከዚህ በፌት ጽሁፍ ያቀረበው ዶ/ር እድሪስ በጽሁፋቸው ሊያነሱት የማይፈልጉት የመንግስት የፖሊሲ ለውጥ ብዙ የሚያስብል ነው፡፡ መንግስት አህባሽን ያመጣው እና አጠቃላይ ሙስሊሙ ላይ እየተገበረ ያለው ተግባር መንግስት ሙስሊሙ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ በጥላቻ እና በደባ ማስኬድ በመጀመሩ እንደሆነ ለመግለጽ አይደፍሩም፡፡ የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ማቆም ነገሮችን ወደ ቦታቸው ይመልሳል የሚሉት ኢሕአዴግን በድሮው መነጽር በመመልከት ነው፡፡ ኢሕአዴግና እየተገበረ ያላቸውን አጠቃላይ ተግባራት ከኢህአዴግ ፖሊሲ አንጻር ለመመልከት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ መንግስት ለአሕባሽ ስልጠና፣ ለሚሰራው ተከታታይ የሚዲያ ዘመቻና ፕሮፖጋንዳ፣ ለሚያዘጋቸው ኢስላማዊ ተቋማት፣ ለሚያስራቸው ሙስሊሞች እና ለእነዚህ ተግባራት የሚያወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር መነሻው ሙስሊሙ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ በጥላቻ እና በሌላ አላማ ምክንያት በመለወጡ እንደሆነ ደፍረው እነ ሀሰን አይነግሩንም፡፡ ይህን የፖሊሲ ለውጥ ጉዳይ ካላነሱ ትግል ስለማቆም ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግስት አሕባሽን ያመጣው ፖሊሲውን ለውጦ ነው፤ አሁንስ ትግላችንን የምናቆመው ይህ ፖሊሲ ተለውጦ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በጣም እንደሚቸገሩ እሙን ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጡ ላይ ያላቸው ምልከታ ነው ለያዙት አቋም ሁሉ መዋዠቅ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረባቸው ያለው፡፡ በዚህ ላይ በስፋት መምጣታችን አይቀርም፡፡
ለሀሰን ሀሳብ በቂ እና አጥጋቢ ምላሽ መስጠት በጣም ቀላል እንደሆነ ፍትህ ታምናለች፡፡ የሀሰንን እናቁም ሀሳብ ትግሉን መቀጠል አለብን በሚል ምላሽ ወደ ቦታው ለመመለስ ሀሰን ጽሁፍ ላይ እንደተንጸባረቀው ብዙ ግምታዊ ነገሮችን ‹‹በይሆናል ብቻ›› ማስቀመጥ አይጠበቅብንም፡፡ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች ትግሉ መቀጠል እንዳለበት በበቂ መልኩ አሳማኝም ናቸው፡፡ እኛ ምላሽ ከመስጠቱ በላይ ግን ሊያሳስበን የሚገባው ለሀሰን ምላሽ ከተሰጠው በኋላ ሀሰን ሊሄድ የሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ወንድም ሀሰን የሚቀርቡበትን ሙግቶች ተመልክቶ ከሀሳቡ ያፈገፍግ ይሆን ወይስ ጀምሬዋለሁና አልተውውም ብሎ ይቀጥልበት ይሆን? ለዛ ፈተና ሁላችንም ራሳችንን እናዘጋጅ፡፡ ወንድም ሀሰን ለእሱ የምንሰጠውን አክብሮትና ፍጹም ወንድማዊ ፍቅር በሌላ መልኩ ሊጠቀምበት እንዳይሞክር አጥብቀን እንማጸነዋለን፡፡ ሀሰንም ኋላ ለሚፈጠረው መዘዝ የታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በአክብሮት እንጠይቀዋለን፡፡ አለሁ አእለም፡፡