ምስጋና የሚገባው ህዝብ!!!

ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ወገቡን አጥብቆ ለሀይማኖታዊ መብቱ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ከገባ ይኸው ሁለት አመት ሊሞላው እየተንደረደረ ነው፡፡ ሁለት የፈተና፣ የመከራ፣ የትግል፣ የበደል፣ ከምንም በላይ ደግሞ የሞራል ልእልና እና የበላይነት የተጎናጸፈበት አመታት ናቸው – የድልም! በዚህ ወቅት ውስጥ ይህ ድንቅ ትውልድ የታዩበት ባህርያት ዛሬ ለምስጋና ብእር እንድንነሳ አስገደደን፡፡ ለዚህ ህዝባችን ምስጋና በቂ ሆኖ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚመሰገንበት ውለታው ብዙ ነው፡፡ ጀዛው አላህ ዘንድ ነው፡፡ ግና መልካም ባህሪዎቹን እየጠቀሱ ጎልተው እንዲወጡ ማድረጉ ታሪካችንን ቀርጾ በማስቀመጡ ረገድ የሚጫወተው ሚና ይኖረዋል፡፡ ህዝባችን መልካም ባህሪዎቹን አውቆ እንዲያሳድጋቸው፣ እንዲያዳብራቸውም ያግዛል፡፡ ከመልካም ባህሪያቱ ንጻሬ ኋላ ደግሞ ድክመቶቹን ተመልክቶ በቻለው እንዲቀርፋቸው በር ይከፍታል፡፡ አንድ አንድ እያልን አብረን እያየናቸው

ህዝባችንን እናመስግን!
አንድነትን የመረጠ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

በትግላችን ውስጥ ጎልተው ከወጡ ህዝባዊ ባህርያት አንዱና ዋነኛው አንድነቱ ነው፡፡ የአህባሽ አደጋ ሙስሊሙን እንዲሰነጣጥቅ ታስቦ የመጣ ነበር፤ ግና የአላህ ፍላጎት ተቃራኒው ሆነና ጠንካራ የአንድነት መሰረት ይኖረን ዘንድ ተቻለ፡፡ ህዝባችን ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የአላህ ስጦታ የሆነው አንድነት መሰረቱ ከበፊቱ ጠንክሮ ይጣል ዘንድ ቀልቡን ለውህደት ከፍቷል፡፡ ጭቅጭቅና ልዩነት ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች በተቻለው በመራቅ በፍጹም መተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ወንድማዊ ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ መጅሊሱና ጸብ የመፍጠር አባዜ የያዛቸው አመራሮቹ በአንድነቱ ላይ የሚያደርጉትን ትንኮሳ በብስለት ዝቅ ብሎ አሳልፏል፡፡ አንድነቱን ለመበተን ያላደረጉት ጥረት፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ ግና አልቻሉም! ባለፉት ሁለት መውሊዶች በሙስሊሙ መካከል ክፍተት ለመፍጠርና ትግሉን ለማኮላሸት ያልተደረገ ጥረት አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ግን ‹‹መውሊድ አይከፋፍለንም›› ሲል አሳፈራቸው፡፡ በተወዳጁ ነቢይ ስም ሙስሊሞችን መነጣጠል እንደማይሳካላቸው አረጋገጠላቸው፡፡ ‹‹ወሐቢያ፣ ሱፊያ›› የሚሉ ስሞች በፓርላማ ጭምር ሲነሱ ሙስሊሙ ግን አንድነትን መርጦ ‹‹እኛ ሙስሊሞች ነን›› አላቸው፡፡ አልሐምዱሊላህ! አንድነታችንን ዘላቂና የጠለቀ ያደርግልን ዘንድ አላህን እንለምነዋለን! ለዚህ ድንቅ ባህሪውም ህዝባችንን እናመሰግናለን!

ህዝባችንን እናመስግን!
የሚረዳዳና የሚተሳሰብ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

ትግሉ ካደመቃቸው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ስነ ምግባራት ውስጥ አንዱ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህሪ ነው፡፡ በዚህ የፈተናና የመስዋእትነት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ሙስሊሙ ድንቅ የመተሳሰብ ባህሪ አሳይቷል፡፡ ወንድም ለወንድሙ ረዳትና ደጋፊ ሆኗል፡፡ ገጠር ውስጥ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ የፖሊስ ዱላ ወይም ጥይት የሚያርፍበት ወንድም የስቃይ ጥሪ መሀል ከተማ ለሚኖሩ ወንድሞቹ ትሰማለች፡፡ ህመሙ በኢንተርኔት መስኮት ሺ ወንድሞቹን ያስጨንቃል፡፡ ‹‹አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል›› እንደሚለው ብሂል በለቅሶና በዱአ ይጠመዳል፡፡ አንዱ መንደር መስጊድ ሲቀማ፣ ወንዶቹ ሲታሰሩበት ሌላው በጾም ባዶ ሆዱን ውሎ፣ ማታ ሰደቃ ሰድቆ፣ ቁኑት ብሎ ዱአ ያደርጋል፤ ወንድሞቹ ከፈተና ይወጡ ዘንድ ወደፈጣሪው አቤት ይላል፡፡ መረጃውን በማሰራጨትና ድምጹን በማሰማት ድጋፉን ይሰጣል፤ ሞራሉን ይለግሳል፡፡ መፍትሄ ፍለጋ ይሯሯጣል፡፡ የታሰረ ካለ ቤተሰቦቹን ይረዳል፤ አልያም ስንቅ ያደርሳል፤ ምናልባት ያን ወንድም ካሁን በፊት አያውቀው ይሆናል… የታሰረበት ጣቢያ ሄዶ ስንቅ ለማድረስ ግን አይሰንፍም! ለምን? ወንድሙ፣ የአላማው ተጋሪ፣ የትግል ጓዱ ነውና! በዘር፣ በስራ፣ በቀለም ሳይሆን በአላማ ነዋ የተሳሰሩት! እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?

ህዝባችንን እናመስግን!
ለመርህ የሚገዛ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

ለመርህ ተገዢነት እና አክብሮት ሌላው የህዝባችን ድንቅ ባህሪ ነው፡፡ ለመርህ ተገዢነት በግለሰብ ላይ ሲታይ ያስደስት ይሆናል እንጂ ብዙ አያስገርምም፡፡ በህዝብ ላይ ሲታይ ግን እጅግ ድንቅ ባህሪ ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በዚህ ረጅም ትግል ውስጥ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሳይቀይር፣ የሚደርስበት ፈተና ሳይበግረው ለፍትህ መስፈን እና ለበደል መወገድ ጠንክሮ ቆሟል፡፡ ከወዲያ ወዲህ እንዳይላጋ በመርህ አክባሪነቱ ላይ እግሮቹን አስምጦ ተክሎ ወጀቡን እየተቋቋመ ቀጥሏል፡፡ የሚያምንበትን እውነታ ለግለሰቦች ባለው ክብር አልለወጠም፡፡ በወጉ የተረዳውን የትግል አላማውን ሀሰትነት ሊያሳምኑት የሞከሩ አልረቱትም፡፡ አዎን! ህዝባችን ሰው መከተልን ትቶ መርህ መከተልን አጥብቆ የመያዝ ባህሪ አዳብሯል፤ ምንኛ ያማረ ባህሪ ነው! እውነትን ከሰዎች ማብለጥ፣ መርህን መለኪያ ማድረግ! እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውምን?

ህዝባችንን እናመስግን!
ለህገ መንግስታዊ መብቱ ዘብ የሚቆም ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

‹‹ለህገመንግስታዊ መብቶቹ መከበር ቆርጦ የተነሳ ህዝብ›› የሚለው ሀረግ ኢትዮጵያዊውን ሙስሊም በሚገባ ይገልጸዋል፡፡ ምስክሮቹ ደግሞ ያለፉት ሁለት አመታት ናቸው፡፡ በነዚህ ሁለት አመታት ሙስሊሙ እንደህዝብ ‹‹መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም›› ሲል ለደነገገው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ መከበር የበኩሉን ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ ሃይማኖታዊ ነጻነታችን እንዲከበር፣ ዜጎች ሀይማኖታዊ ስብእናቸው ሳይሸራረፍ በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ታግሏል፡፡ በንግግር ብቻ አይደለም – ይልቁንም በሙሉ ተነሳሽነት ድምጹን እያሰማ፣ ለመብቱ በአደባባይ እየዋለ፣ ደሙን እየገበረ ነው የታገለው፡፡ እውን ለዚህ ውለታው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?
ለመብቱ በተግባር የሚታገል ህዝብ ምስጋና ይገባዋል!

ሰዎች ስለመብታቸው ያውቃሉ፤ ያወራሉ፣ ይፅፋሉ፤ እኒህ ሁሉ ተግባራት ትርጉም የሚኖራቸው ግን መብቱን የሚያውቅ ትውልድ መብቱን አጠንክሮ የሚጠይቅ ትውልድ ሲሆን ነው፡፡ ህዝባችን በዚህ በኩል ሊታይ የሚችል ስራ ሰርቷል፡፡ መብት የሚገኘው እያወሩ እጅን አጥፎ በመቀመጥ ሳይሆን ከምንም በላይ በተግባር ለመብት በመታገል፣ ለበደል ባለማጎብደድ እንደሆነ ያለጥርጥር አረጋግጧል፡፡ ብሶታቸውን በ‹‹እህህ››ታ የሚያሳልፉ በበዙበት፣ የፍርሀት ቆፈን ልቦችን በጨመደደበት፣ ዝምታ ሰዎችን በዋጠበት ከባቢ ውስጥ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የሚል የፍትህ ጥሪውን አስተጋብቷል፡፡ ህዝባችን ይህን ሲያደርግ በርካታ ተስፋ አስቆራጭ እርምጃዎች እየተወሰዱበት፣ በየሳምንቱ የሚያሰማው ውድ ድምጹ በአሳፋሪ ሁኔታ ችላ እየተባለበት ነው፡፡ ግና ይህ ሁሉ ተስፋ አላስቆረጠውም፤ ድልን ከፊቱ እያየ መስዋእትነት ከመክፈል አላገደውም፡፡ ለነገ ብሩሀማነት ዛሬውን ለአፍታ ማጨለም አልገደደውም፡፡ እርግጥ ትግሉ ገና አልተጠናቀቀ ይሆናል፡፡ ውጤቱ ከነሙሉ ወዙ ለመታየት አልደረሰ ይሆናል፡፡ የሚሰጠው ትምህርት ግን የዋዛ የሚባል አይደለም፡፡ መብቱን የሚያውቅና የሚጠይቅ ትውልድ ድል መጎናጸፉ አይቀርም፡፡ በዙሪያው ላሉት ሁሉ ትምህርት ይሰጣል – ለበዳይም ሆነ ለተበዳይ፡፡ የበደልን የእድሜ ዑደት ይቆርጣል፡፡ የበዳዮችን ግርማ ይሰልባል፡፡ የዚህ ታጋይ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ትውልድ አባል በመሆናችን ልንኮራ ይገባናል፡፡ እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?

ህዝባችንን እናመስግን!
ታጋሽና ሰላማዊ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

‹‹ታጋሽና ሰላም ወዳድ፣ እጅግ ሰላማዊ›› እንበለው ህዝባችንን፤ ይገልጸዋል፡፡ ፍጹም ሰላማዊ ነው፡፡ ሁከትን አይፈልግም፤ ብጥብጥ አያምረውም፡፡ ለሰላማዊ ትግል መርሁ ምን ጊዜም ተገዢ ነው፡፡ ድምጹን ለማሰማት የሚሰበሰበው በብሄራዊ ደረጃ፣ በሚሊዮኖች ቁጥር ሆኖ ነው፡፡ በአገሪቱ ሁሉም አቅጣጫዎች ሁልቆ መሳፍርት ሆኖ የፍትሕ ጥሪውን ያሰማል፡፡ በዙሪያው የህዝብ ብዛት አለ፤ ግን ነሻጣ አያሸንፈውም፡፡ በዙሪያው ድንጋይ አለ፤ ግን መወርወር አያምረውም፡፡ በዙሪያው መስተዋት አለ፤ ግን መስበር አያምረውም፡፡ ፍጹም ሰላማዊ ነው! ጥፋት የማድረስ ዝንባሌ በውስጡ የለም፡፡ የሚንተገተግ ቁጣውን የሚገልጸው በፍጹም ስርአትና ስነ ምግባር ነው፡፡ አገሩን ይወዳልና የህዝብ ንብረት አያጠፋም፡፡ ድንጋይ ሲወረውር ቀርጸው የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሊያደርጉት አሰፍስፈው የሚጠብቁትን ካሜራዎች አሳፍሮ ይመልሳቸዋል፡፡ ወደነውጥ ቢገባ ሊደርስ የሚችለውን አገራዊ ቀውስ ይረዳልና ሁሌም ሰላማዊ ነው፡፡ የማይፈጸምበት በደል ባይኖርም ህዝባችን ግን ታጋሽ ጀግና ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ መብቱ ተጥሷል፤ የማይፈልገውን ሀይማኖት እንዲቀበል በመንግስት ተጠይቋል፤ የሃይማኖት ተቋሙ በካድሬዎች ተወስዷል፤ መሳጂዶቹ ለመጤ አስተምህሮ ፊዳ ተደርገዋል፤ በደሉን አቤት ይሉለት ዘንድ መርጦ የላካቸው ወኪሎቹ ተለቅመው ታስረዋል፤ ዳኢዎቹና ኡለሞቹ ዘብጥያ ወርደዋል፤ ሚዲያና ልሳኖቹ ተከርችመዋል፣ ወጣት ሴትና ወንዶቹ በየጁሙአው ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተደብድበዋል፤ ተዘርፈዋል፤ ተገድለዋል፡፡ ይህ ሁሉ በደል ደርሶበት ግን ታጋሽነትና ሰላማዊነቱ ፍንክች ሳይል ሁለት አመት ሊሞላው ነው፡፡ በበደል ውርጅብኝ መሀል እንዲህ የሚታገስ፣ እንዲህ የሰላማዊነት ካባ የሚጎናጸፍ ትውልድ አይተዋልን? ጠመንጃ ለወደሩበት ‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም›› የሚል ጨዋ ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?

ህዝባችንን እናመስግን!
ደፋርና ጀግና ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

ሌላው አስደናቂ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባህሪ ድፍረትና ጀግንነት ነው፡፡ ትግሉ ተጀምሮ መካረር ደረጃ ከደረሰበት የካቲት 26/2004 ጀምሮ መንግስት ትግሉን ለማስቆም ሲሰነዝራቸው የነበሩት ማስፈራሪያዎች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ተቃውሞው ወደ አንዋር ከተዛወረ ጀምሮ ከፍተኛ ዛቻ ተሰንዝሮበታል፡፡ ነገር ግን የ‹‹እርምጃ እንወስዳለን›› ማስፈራሪያዎች ህዝባችንን አልበገሩትም፤ ከህጋዊ የመብት ትግሉ አላገዱትም፡፡ የአንድነትና የሰደቃ ፕሮግራሞቹን ለማስቆም በየከተሞቹ የተሰነዘረው አስተዳደራዊ ዛቻ በጣም ከባድ ነበር፤ ሊሻገረው ግን አላቃተውም ለህዝባችን፡፡ በአወሊያ፣ በደሴ፣ በአሳሳ፣ በገርባ፣ በሻሸመኔ፣ በአዳማ፣ በአጋሮና በሌሎችም ከተሞች ህዝባችንን ለማሸማቀቅ የተወሰዱ የሀይል እርምጃዎችም ሆኑ ዛቻዎች ከአላማው አላስቆሙትም፡፡ እስካሁን ድረስም ዛቻውን ከመጤፍ ሳይቆጥር የመርህ ትግሉን ቀጥሏል፡፡ ሊያሸማቅቁት በጣሩ ቁጥር ሞራሉ የሚጨምር፣ በየጁምአው የሚያርፍበት የፖሊስ ዱላና የሚጋዝበት እስር የማያስፈራው፣ ተደጋጋሚ ዛቻ ድምጹን ከማሰማት የማያግደው፣ የግፈኞች ድምጽ የማያርበደብደው ህዝብ ነው ህዝባችን፡፡ እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?

ህዝባችንን እናመስግን!
ለፕሮፓጋንዳ የማይንበረከክ ህዝብ ምስጋና ይገባዋልና!

ህዝባችን ለፕሮፓጋንዳ የማይንበረከክ ህዝብ ነው፡፡ መንግስት ኢቲቪና ፋናን በመሳሰሉ የፕሮፓጋንዳ ማሽኖቹ በህዝበ ሙስሊሙ ዙሪያ የሚነዛውን አደገኛ ፕሮፓጋንዳ አምክኗል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙን እንደ አገር ጠላት አድርገው የሚስሉ፣ ሚሊዮኖችን በአክራሪነትና አል ቃይዳነት የሚፈርጁ፣ በሽብርተኝነት የሚከሱ የፕሮፓጋንዳ ዜናዎችንና ፊልሞችን መሰናክል ተሻግሯል፡፡ ለሚረጩት ሐሰት ጆሮውን ነፍጓል፡፡ በኢድና አረፋ ሰልፎቹ ደጃቸው ድረስ ሄዶ ማንነታቸውን ነግሯል፡፡ በመቻቻልና አብሮ መኖር ባህሪው ፍፁም ተቃራኒ ፕሮፓጋንዳቸውን እርቃን አስቀርቷል፡፡ ከእውነት ማማ ላይ ሆኖ ከፍ ባለ ድምጹ አላማውን አስረድቷል፡፡ የበደል ጥሪውን አሰምቷል፡፡ በዚህም በሌላ ሃይማኖት ተከታዮችም ሆነ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በትክክለኛ መብት ጠያቂ ገጽታው መታየትና ድጋፍ ማግኘት ችሏል፡፡ መንግስት ሊከምርበት ከሚፈልገው የሐሰት ቁልል ልቆ መታየትና ተቀባይነት ማግኘት ችሏል፡፡ ይህን ማሳካት የቻለው ደግሞ ካሁን ቀደም ተመሳሳይ ልምድ ሳይኖረውና በአገራችን ታሪክ ምሳሌ አድርጎት ሊነሳበት የሚችለው ስኬታማ የሰላማዊ ትግል ታሪክ ሳይኖር መሆኑ ይበልጥ እውነታውን ያጎላዋል፡፡ እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪው ህዝባችን ሊመሰገን አይገባውም?

ህዝባችንን እናመስግን!
ጀግኖች ሴት ታጋዮቻችን ምስጋና ይገባቸዋልና!

ጠንካራና አስገራሚ የሴቶች ተሳትፎ የህዝባችን ሌላው ጠኝካራ ገጽታ ነው፡፡ ሴቶች በባህል ምክንያት የነበራቸው ህዝባዊ ተሳትፎ ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ይህንን ትርጉም ባለው መልኩ እንደ ህዝብ መለወጥ ችሏል ህዝባችን፡፡ ትግላችን ከተጀመረ አንስቶ ሙስሊም ሴቶች ያደረጉት ተሳትፎ ወደር የለሽ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ትግላችን ሰላማዊ መሆኑ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ የፈተና ወቅት ሙስሊም እህቶቻችን ለዲናቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት በሚገባ አስመስክረዋል፡፡ በጁምአ ተቃውሞዎች ላይ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ህብረተሰቡን ያነቁት የሰደቃና አንድነት ፕሮግራሞች ያለሴት እህቶቻችን ደማቅ ተሳትፎ ስንዝር እንኳ መራመድ ባልቻሉ ነበር፡፡ የእህቶቻችን ድምጽ ባልተቀላቀለበት ኖሮ የፍትህ ጥሪያችን ጎዶሎ በሆነ ነበር፡፡ በኢስላም የመጀመሪያዋን ሸሂድ ሱመያን የሚያስታውሱን ጀግኖች እህቶቻችን ድምጻችንን ባሰማንባቸው ወቅቶች ሁሉ ከጎናችን ነበሩ፡፡ ስንገረፍ ተገርፈው፣ ስንደበደብ ተደብድበው፣ ስንታሰር ታስረው፣ ስንደማ ደምተው ትግላችንን አጠናክረዋል፡፡ ለኢስላም የሚሰስቱት ህይወት እንደሌላቸው አረጋግጠዋል፡፡ እውን ለዚህ ድንቅ ባህሪያቸው ውድ እህቶቻችን እናቶቻችን ሊመሰገኑ አይገባቸውም?

ጀዛኩሙላሁ ጀሚዓኒል ኸይራ!

ታላቁ ነቢይ ሙሀመድ (ሰዐወ) ‹‹ሰዎችን ያላመሰገነ አላህን አያመሰግንም›› ይላሉ፡፡ እናም እናመስግን፡- ህዝባችን ሊመሰገን የሚገባው የድንቅ ትውልድ አካል ነው፡፡ እናመሰግናለን! ግና ምስጋናን በመሻት ሳይሆን የአላህን ውዴታ ሽቶ ለዲኑ መነካት ጥብቅና እንደቆመ እናውቃለንና አላህ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ምንዳ እንዲያበዛ፣ ድሉንና የመብቱን መከበር እንዲያቀርብልንና ፈተናውን እንዲያሳጥርልን የሁልጊዜ ዱአችን ነው፤ ሊሆንም ይገባል፡፡ ኢስላም ያስተማራቸውን መልካም ተግባራት በመፈጸም አላህ በትግላችን ስኬታማ እንዲያደርገን ሁላችንም እንበራታ! ይበልጥ ተጠናክረን እንቀጥል፡፡

ይህ ምስጉን ታሪካዊ ትውልድ ነገም ሁሌም ታሪክ መስራቱን ይቀጥላል! ሁላችንም የዚህ ትውልድ አካል በመሆናችን እንኮራለን፡፡

አላሁ አክበር!