የህዝበ ሙስሊሙ ትግል ይቀጥላል

[Radio Negashi/ሬድዮ ነጋሽ] በ16ኛው መቶ ክፍለዘመን ሰሜን ኢትዮጵያን የገዛው አፄ ሶሶኒዮስ ከፖርቱጋል ከመጡ የካቶሊክ እምነት ሰባኪዎች ጋር ወዳጅነት በመፍጠርና ከኃያሉዋ ፖርቱጋል ጋር መዛመድ የስልጣን እድሜዬን ለማራዘም ይረዳኛል በሚል ራእይ የኦርቶጎክስ እምነቱን በመተው ወደ ካቶሊክ እምነት ከገባ በኃላ ህዝቡም እርሱን ተከትሎ ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲገባ ት እዛዝ አስተላለፈ። ከህዝቡና ከቀሳውስቱ የተወሰኑት የንጉሱስን ትእዛዝ በማክበር ኃይማኖታቸውን ሲቀይሩ ከህዝቡም ከቀሳውስቱም የሚበዙት ግን አሻፈረኛ በማለት ንጉሱ ላይ አመጹ። ሶሶኒዮስ አመጹን ለመግታት የብዙዎችን ደም አፈሰሰ፤ ህይወትም ቀሰፈ። ያም ሆኖ ግን ያሰበው ሳይሳካለት ቀኑ ደረሰና ወደ ፈጣሪው ተጠራ። ሶሶኒዮስን ተከትሎ ልጁ ፋሲለደስ ነገሰ። ፋሲለደስ የሥልጣን በትሩን እንደጨበጠ አባቱ ይከተል የነበረውን ዜጎችን በኃይል እምነት የማስቀየር የተሳሳተ ፖሊሲና ዘመቻ በመቀየር ህዝቡ ወደ ቀድሞው እምነቱ እንዲመለስ ፈቀደ። አመጹ ቀረ፤ ሠላምም ሰፈነ።

ይህንን የፄዎች የታሪክ ቅንጫቢ የተረክነው ያለ ምክንያት አይደለም። አሁን ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ካለበት ሁኔታ ጋር የሚያመሳስለው ነገር ቢኖር እንጂ። በቅርቡ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠ\ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሙስሊም ዜጎችን እርሳቸው በምዕናባቸው በፈጠሩት አምሳል ለመቅረጽ በማሰብ አዲስ እምነት ከሌባኖስ በማስመጣት ህዝበ ሙስሊሙ እንዲጠመቅ ት እዛዝ አስተላለፉ። ከህዝቡም ከመሻኢኮቹም የተወሰኑቱ የአቶ መለስን ትእዛዝ በማክበር አዲስ ሸሀዳ ሲያዙ ከህዝቡም ከመሻኢኮቹም የሚበዙት ግን አሻፈረኝ በማለት ተቃውሞዋቸውን በአደባባይ አሰሙ። አቶ መለስ ተቃውሞውን ለመግታት ብዙ ደም አፈሰሱ፤ ህይወትም ቀሰፉ። ያም ሆኖ ግን ያሰቡት ሳይሳካላቸው ቀናቸው ደረሰና በድንገት ወደ ፈጣሪያቸው ተጠሩ። በቦታቸውም አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተተኩ። በሶሶኒዮስ – ፋሲለደስና አቶ መለስ – ኃይለማሪያም መካከል ያለውም ተመሳሳይነት እዚሁ ላይ አከተመ። ንጉሱ ፋሲለደስ የአባቱን ስህተት በማረም በግዛቱ ውስጥ ሠላምን ሲያሰፍን አቶ ኃይለማሪያም ግን የአቶ መለስን የተንሸዋረረ ራእይ የሙጥኝ አሉ። ሠላምም አልመጣም፤ ተቃውሞውም ቀጠለ።

አቶ መለስ በድንገት ወደ ላይኛው ቤት ሲጠሩና በአቶ ኃይለማሪያም ሲተኩ ብዙዎች መልካም ነገር ጠብቀው ነበር። አቶ መለስ የጀመሩትና የሙስሊሙን መብት ክፉኛ የተተናኮለ እርምጃ አግባብነት የሌለውና ገዢውንም ፓርቲ የሚጎዳ እንደሆነ ለብዙዎች ግልጽ በመሆኑ አቶ ኃይለማሪያም መምህራቸው የፈጸሙትን ስህተት በማረም ከሙስሊሙ ጋር አዲስና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር የአቶ መለስ በድንገት መሞት የፈጠረውን የእድል መስኮት ይጠቀሙበታል የሚል እምነት ብዙዎች ላይ አድሮ ነበር። አቶ መለስ የጀመሩት የሙስሊሙን እምነት የማስቀየር ዘመቻና ዘመቻውን ተከትሎ ከመስሊሙ የተሰጠው ምላሽ ያረጋገጠው ሀቅ በአቶ መለስ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ሙስሊሙ ያለውን እጅግ የተወላገደ አመለካከት ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙን የንቃተ ህሊና ደረጃም ጭምር ነበር። ሙስሊሙ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ ሠላማዊና ቆራጥ የትግል ዘዴን ተገበረ። የመንግስት እርምጃ ህገመንግስቱን የተጻረረ መሆኑን መሰከረ። መንግስት በኃይማኖት ጉዳይ ገብቶ የመፈትፈት መብት የለውም፣ እምነት የአማኞቹ ጉዳይ ስለሆነ ለአማኞቹ ሊተው ይገባል ሲሊም በአደባባይ አወጀ!

ሙስሊሙን በአህባሽ እምነት የማጥመቅ ዘመቻ በመንግስት በይፋ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አስራሁለት ወራት ሙስሊሙ የጁመዓ ሠላትን ተከትሎ ተቃውሞውን በተከታታይ በሠላማዊ መንገድ አሰማ። መሪዎቻችንን ራሳችን የመምረጥ መብታችን ይከበር፣ አዲስ እምነት በግድ አይጫንብንና እስላማዊው ኮሌጅ አወሊያ የህዝብ ንብረት እንደመሆኑ ወደ ህዝቡ ተመልሶ በቦርድ ይተዳደር የሚሉ ጥያቄዎቹን አነሳ። እነኝህንም መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎቹን ይዞ ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር የሚደራደር አንድ ባለ አስራሰባት አባላት ኮሚቴም አቋቋመ።

የአቶ መለስ ዜናዊ መንግስት ግን ለሙስሊሙ ሠላማዊ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ልክ እንደ አፄው ሀይልን ተጠቅሞ እንቅስቃሴውን ለመደምሰስ መሞከር ነበር። የደህንነት ኃይላት ህዝብን ከጥቃት ለመከላከል በሚል የታጠቁትን መሳሪያ የህዝብን ድምጽ ለማፈን ተጠቀሙበት። ህዝብን ከወንጀለኞች ለመጠበቅ በሚል የተገነቡትን ማረሚያ ቤቶች ሠላማዊ ዜጎች አጣበቧቸው። ለህዝቦች መብት መከበር ቆሚያለሁ የሚለው መንግስት መብታቸውን የጠየቁ ህዝቦችን በአስለቃሽ ጪስ አቃጠላቸው፣ በቆመጥም ያለ ርህራሄ ቀጠቀጣቸው። ዜጎች የመቃውም ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተገፎ በጅምላ ታፍሰው በየማረሚያ ቤቱ ታጎሩ። እዚያም የተለያዩ አይነት ሰቆቃዎች ተፈጸሙባቸው። የህዝቡን የመብት ጥያቄዎች ለመንግስት ባለሥልጣናት እንዲያደርሱ በህዝብ የተመረጡ የኮሚቴ አባላትም ታፍሰው ማረሚያ ቤት ተጣሉ።

ያም ሆኖ፣ ይህ ሁሉ የመንግስት ኢ-ሰብአዊ እርምጃ ትግሉን አላስቆመውም። የዚህ ስንኩል ራዕይ ደራሲ የነበሩት ጠ\ሚኒስትርም በድንገት አረፉ። አቶ ኃይለማሪም ደሳለኝ በእግራቸው ተተኩ። እሳቸውም ከኃላዬ እያንደረደራችሁኝ ከፊቴ ደግሞ ከረባቴን እየጎተታችሁኝ የቀድሞ አለቃዬ በተጓዝኩበት ጎዳና ምሩኝ ሲሉ ተማጸኑ። የቀድሞው ጠ\ሚኒስትር ቀብር ተፈጽሞ ባንዲራውም ወደ ቀድሞ ቦታው ከመመለሱ ሙስሊሙ ላይ የተጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ቀጠለ። እስርና ግርፋቱም እንዲሁ። የአቶ መለስ እንጂ የራሳቸው የሆነ ምንም ራእይ እንደሌላቸው ያለምንም እፍረት በህዝብ ፊት የመሰከሩት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፓርቲያቸው በሙስሊሙ ላይ የያዘውን የተንሻፈፈ ፖሊሲ ይዞ መጓዙን እንዲቀጥልበት ፈቀዱ። ሙስሉሞች ሊሳተፉበት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ ያወጁበት የመስጂድ ምርጫ በውድም በግድም፣ በሙስሊሙ ተሳትፎም ሆነ ያለ ሙስሊሙ ተሳትፎ እንዲካሄድ ወሰኑ። ህዝበ ሙስሊሙ ከተቻለ በማባበያ አለበለዚያም በማስፈራሪያ ለምርጫ እንዲመዘገብ ግዳጅ ተጣለበት። ጥቂቶች ተመዘቡ፤ ብዙዎች ግን የመጣው ይምጣ ብለው ላለመመዝገብ ወሰኑ።

ኢህአዴግ የፓርቲ አባላቱን ኃይማኖት ሳይመርጥ አስመራጭና መራጭ እንዲሆኑ በየቀበሌው አሰማራ። ምርጫም ተደረገ። ቀደም ተብሎ እንደተፈራውም የሙስሊሙ ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኘ። ሌላው ቀርቶ በፍርሀት ተመዝግበው የነበሩት እንኳን በምርጫው እለት ሳይገኙ ቀሩ። ነገሩን ቀድሞውንም ጠርጥሮ የነበረው መንግስት የምርጫ ካርድ እንኳን ባለማዘጋጀቱ እገሌን የምትፈልጉ እጅ አውጡ በማለት ካድሬዎቹን በካድሬዎቹ አስመጦ ጨዋታው አበቃ።

ይህ ማለት ትግሉ አበቃ ማለት ይሁን አይሁን ወደፊት የምናየው ይሆናል፤ ነገር ግን ሙስሊሙ ለምርጫው ከሰጠው እጅግ አነስተኛ ግምትና መብቱን ለማስከበር እያሳየ ካለው ቁርጠኝናት ተነስተን ስንመረምረው ትግሉ በበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመገመት የሚከብድ አይሆንም። መንግስት ሙስሊሙን ለማዳከምና በመካከላቸው ክፍፍልን ለመፍጠር በማሰብ አንዳንድ በመልካም ስብእናቸው የሚታወቁ ግለሰቦችን በውድም በግድም ምርጫው ላይ እንዲሳተፉና እንዲመረጡ እንዳደረገ ሰምተናል። አንዳንድ ቀድሞ በአንድ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ ወንድሞችም በአካሄድ ላይ በፈጠሩት ልዩነቶች ሳቢያ የተለያዩ አቁዋማትን የያዙበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል። መንግስትም ይህንን ቀዳዳ ተጠቅሞ ልዮነቱን ለማስፋትና ወደማይታረቅ ቅራኔ ለመቀየር የሚችለውን በሙሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ስለዚህ ይህ የመንግስት እኩይ አላማ እንዲከሽፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ልክ ቅንጅት ላይ እንደሆነው፣ የቀድሞ ወዳጆች ጎራ ለይተው ሰብዕናን የሚነኩ ቃላትን ከመወራወር ሊቆጠብ ይገባል እንላለን። አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም በእስር ላይ የሚገኙ መሪዎቹንና በእነሱ ተወክለው እየተንቀሳቀሱ ያሉትን መሪዎች በመከተል ወደ ድል ጎዳና የሚወስደውን ረጂም መንገድ ለመጓዝ ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ታዲያ በዚህ ጉዞ መካከል የአንዳንድ ወገኖች መንገድ ላይ መንጠባጠብ አይቀሬ መሆኑን ተረድተን መንገድ ላይ ቆመን እርስ በርስ በመጨቃጨቅ ጊዜን ከማባከን ይልቅ ጉዞአችንን መቀጠሉ የተሻለው አማራጭ ነው እንላለን፤ አላሁ አለም!